ኢትዮጵያ ካላት የቱሪዝም መስህብ አኳያ ከዘርፉ የሚጠበቀውን ያህል ጥቅም እያገኘች አይደለም ተባለ

88
አዲስ አበባ ጥቅምት 29/2011 ኢትዮጵያ ካላት የቱሪዝም ኃብት አኳያ ከዘርፉ የሚጠበቀውን ያህል ጥቅም እያገኘች አይደለም ተባለ። የቱሪዝም ዘርፉን ለማሻሻልና የሚጠበቀውን ያህል ጎብኚ ለማምጣት በዘርፉ የተሰማራውን የሰው ኃይል እውቀትና ክህሎት ለማሳደግ የሚያስችል ተከታታይ ስልጠና መስጠት እንደሚገባ ተገልጿል። የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በአገር አቀፍ ደረጃ በአስጎብኚነትና በ'ቱር ኦፕሬተር'  ስራ ላይ ተሰማርተው ለሚገኙ 172 ባለሙያዎች ለአራት ቀናት የቆየ ስልጠና ሰጥቷል። ስልጠናው የተዘጋጀው አስጎብኚዎችን ጨምሮ በዘርፉ የተሰማሩትን ባለሙያዎች እውቀትና ክህሎት ለማሳደግ ታስቦ ነው ተብሏል። በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የቱሪስት አገልግሎቶች ብቃት ማረጋገጫና ደረጃ ምደባ ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ ደርበው በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፣ ስልጠናውን ያገኙት አስጎብኚዎችና 'ቱር ኦፕሬተሮች' በዋናነት በዘርፉ ላይ የሚስተዋለውን ክፍተት ለመቀነስ ያግዛሉ። የቱሪዝም ዘርፉን ማህበረሰብ ተኮር ለማድረግና በዘርፉ ላይ ተሰማርተው የሚገኙትን ባለሙያዎች በመረጃ የበለጸጉ ለማድረግም ይረዳቸዋል ነው ያሉት። አገሪቱ ከዘርፉ በአግባቡ መጠቀም ትችል ዘንድ በመስኩ ለተሰማሩት ሙያተኞች የሚሰጠው እንዲህ አይነቱ ስልጠና ተከታታይነትና ወጥ በሆነ መልኩ መቀጠል እንዳለበትም አሳስበዋል። አቶ ካሳሁን ወርቁ ለ16 አመታት በግላቸው በአስጎብኚነት ስራ ላይ ተሰማርተው የሚገኙ ሙያተኛ ሲሆኑ፣ኢትዮጵያ ካላት የቱሪስት መስህብ አኳያ መጠቀም የሚገባትን ያክል እየተጠቀመች እንዳልሆነ ይስማማሉ። በዘርፉ ከሚስተዋሉት ተግዳሮቶችም መካከል አንዱ አስጎብኚዎችና 'ቱር ኦፕሬተሮች ' የሙያ ክህሎት እጥረት ሲሆን ይህንንም ችግር ለመፍታት እንዲህ አይነት ስልጠናዎች እንደሚያስፈልጉ ተናግረዋል። አስጎብኚዎች የአገር አምባሳደሮች በመሆናቸው የተሰጣቸውን ትልቅ ኃላፊነት በማወቅ አገራቸውን በዘርፉ ለማስተዋወቅ በየጊዜው እራሳቸውን በመረጃ ማደስ እንዳለባቸውም ገልጸዋል። የአዲስ አበባ አስጎብኚ ድርጅቶች ማህበር ፕሬዝዳት አቶ ናሆም አድማሱ በበኩላቸው ብዙ አስጎብኚዎች በስራቸው ላይ የሙያ እና የመረጃ ክፍተቶች ይስተዋሉባቸው እንደነበር ጠቅሰዋል። ለአራት ቀናት የተሰጠው ስልጠና ችግሮቹን ለመቀነስ እንደሚያስችል እምነት እንዳላቸውም ተናግረዋል። ስልጠናው ከአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ በተውጣጡ ምሁራን የተሰጠ ሲሆን በኢኮሎጂ፣ በጂኦሎጂ፣ በማህበረሰብ አቀፍ ቱሪዝምና የኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር ዙሪያ ያተኮረ ነበር ተብሏል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም