የአንድ ገጽ እቅዱ ጠንካራ የግልጸኝነትና የተጠያቂነት ስርዓት እንደሚያሰፍን ተገለጸ

2218

አዲስ አበባ ጥቅምት 29/2011 የመንግስት የአንድ ገጽ እቅድ ጠንካራ የግልጸኝነትና የተጠያቂነት ስርዓት እንደሚያሰፍን ተገለጸ።

መንግስት “ኢትዮጵያ አዲስቷ የተስፋ አድማስ” በሚል መሪ ሃሳብ የአንድ ገጽ እቅዱን በቅርቡ ይፋ ማደረጉ ይታወሳል።

መሪ ሃሳቡ ኢትዮጵያ የጀመረችውን ለውጥ፣ ለውጡ ይዞት የመጣውን ተስፋ እንዲሁም እቅዱ በግልጽ ቋንቋ መቅረቡ እንደ አድማስ ሁሉም ዜጋ ካለምንም ገደብ እንዲመለከተው ማድረጉን የሚገልጽ ነው።

እቅዱ በዋናነት መንግስት እስከ 2012 ዓ.ም ምርጫ ድረስ እሰራቸዋለሁ ያላቸውን ተግባራት የያዘ ሲሆን፤  ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶችም የቀረበውን እቅድ መሰረት በማድረግ የየራሳቸውን የአንድ ገጽ እቅድ ያዘጋጃሉ።

በጠቅላይ ሚንስትር ልዩ ጽህፈት ቤት ከፍተኛ የፖሊሲ አማካሪ አቶ ማሞ ምህረት እንዳሉት፤ በመንግስት የተዘጋጀው የአንድ ገጽ እቅድ ዴሞክራሲና የህግ የበላይነት እንዲሁም የስራ እድል ፈጠራና ተወዳዳሪነት ላይ ትኩረቱን አድርጓል።

እቅዱ አንድ ገጽ ከመሆኑ በላይ አገራዊ ፍላጎትና አቅምን ባጣጣመ መልኩ የተዘጋጀ መሆኑን አክለዋል።

በጽህፈት ቤቱ የህግ አማካሪ አቶ አበበ አበባየሁ በበኩላቸው እቅዱ በአንድ ገጽ መቅረቡ ዜጎች የእቅዱን አፈጻጸም በቀላሉ በመገንዘብ መንግስትን ተጠያቂ እንዲያደርጉ እንደሚያግዝ  ይናገራሉ።

ከዚህ በፊት እቅዶች በብዙ መቶ ገጾች የሚዘጋጁ በመሆናቸው ለተገልጋዮች ለማስረጽና ለመመዘንም አስቸጋሪ እንደነበር የተናገሩት ደግሞ የቀድሞ የጽህፈት ቤት ኃላፊና የአሁኑ የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ፍጹም አረጋ ናቸው።

የአንድ ገጽ እቅዱ ዋና ዋና የተባሉት ተግባራት ላይ ብቻ ትኩረት ለማድረግ እድል እንደሚፈጥር ገልጸው፤ እስከ ታችኛው የመንግስት እርከን ያሉ ተቋማት መሰል እቅድ እንደሚያዘጋጁ አብራርተዋል።

የእቅዱ መዘጋጀት የመንግስት የልማት አጋር አገራትም ሆኑ ድርጅቶች ምን እና እንዴት ድጋፍ ማድረግ እንዳለባቸው በቀላሉ እንዲረዱት እንደሚያስችልም አክለዋል።