ኢትዮጵያና ሳን ማሪኖ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ለመጀመር ተስማሙ

1104

አዲስ አበባ ጥቅምት 29/2011 የኢትዮጵያና የሳን ማሪኖ ሪፐብሊክ መንግስታት ይፋዊ የዲፕሎማሲ ግንኙነት መጀመር የሚያስችላቸውን ስምምነት ተፈራረሙ።

ስምምነቱን በኢጣልያ የኢትዮጵያ አምባሳደርና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቋሚ መልዕክተኛ ወይዘሮ ዘነቡ ታደሰ እና በኢጣልያ የሳን ማሪኖ አምባሳደር ዳኔላ ሮቶንዳሮ ትናንት በሮም መፈራረማቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።

በፊርማ ስነ-ስርዓቱ ሁለቱ አምባሳደሮች ኢንቨስትመንት፣ ንግድ፣ ቱሪዝምና የባህል ልውውጥን ጨምሮ የአገሮቹን ሁለገብ ግንኙነት አጠናክሮ ለማስጀመር ተስማምተዋል።

በአሁኑ ወቅት በኢጣልያ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ሳን ማሪኖን ጭምር ሸፍኖ የሚሰራ ሲሆን በተመሳሳይ በኢጣልያ የሳን ማሪኖ ኤምባሲ የሁለቱን አገሮች ዲፕሎማሲያዊ ጉዳዮች እንደሚሸፍን ከጽህፈት ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ኢትዮጵያ ዘመናዊ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲና የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመረችው በአጼ ኃይለስላሴ ዘመን እንደሆነ የታሪክ አጥኚዎች ይገልጻሉ።

ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ፣ ከአውሮፓ፣ ከሰሜንና ደቡብ አሜሪካ፣ እንዲሁም በእስያ አህጉር የሚገኙ አገራት ጋር የጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ የዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በማድረግ ላይ ትገኛለች።

የቆዳ ስፋቷ 61 ነጥብ 2 ኪሎ ሜትር ስኩዌር የሆነው አውሮፓዊቷ ሳን ማሪኖ 33 ሺህ 400 ህዝብ የሚኖርባት ሲሆን በህዝብ ብዛትና በቆዳ ስፋት በዓለም አምስተኛ ትንሿ አገር ናት።