“ኢትዮጵያ የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ለማሳደግ እየሰራች ነው” ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ

1278

አዲስ አበባ ጥቅምት 29/2011 በደቡብ አፍሪካ ጆሃንስበርግ እየተካሄደ በሚገኘው በአፍሪካ የኢንቨስትመንት ፎረም ላይ በመሳተፍ ላይ የሚገኙት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ  ኢትዮጵያ የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ለማሳደግ እየሰራች እንደሆነ ተናገሩ።

ፕሬዚዳንቷ በፎረሙ ላይ ለመሳተፍ ትናንት ወደ ስፍራው ማቅናታቸው ይታወቃል።

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ መንግስት በኢትዮጵያ የምጣኔ ሃብት ግንባታ ሂደት ውስጥ የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ ለማሳደግ የሰጠውን ትኩረት በሚመለከት በፎረሙ ላይ ገለጻ እያቀረቡ ነው።

በኢትዮጵያ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለማሳደግ ዘርፈ ብዙ ስራዎች መከናወናቸውን የጠቀሱት ፕሬዚዳንቷ በአገሪቱ ተገንብተው የተጠናቀቁና በግንባታ ሂደት ላይ የሚገኙ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በማሳያነት መግለጻቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።

መንግስት ወጣቶችን በ50 ዩኒቨርሲቲዎችና በተለያዩ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት በማሰልጠን ለኢንቨስትመንት ምቹ የሆነ የሰው ሃይል ለማፍራት እየሰራ መሆኑንም ፕሬዚዳንቷ ገልጸዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ በቆይታቸው ከደቡብ አፍሪካ መሪዎች ጋር ይነጋገራሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን በኢንቨስትመንት ፎረሙ ላይ ኢትዮጵያ ያላትን ምቹ የኢንቨስትመንት እድል እና ተሞክሮ  ያስተዋውቃሉ ተብሏል።

ፎረሙ በዋናነት የአፍሪካ የኢንቨስትመንት አማራጮችን በአግባቡ በመጠቀም የአህጉሩን የልማት ውጥኖች ለማሳካት በሚቻልባቸው አማራጮች ላይ ምክክር የሚያደርግ ነው።

በጉባኤው ላይ ዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማትና ተያያዥነት ያላቸው አካላት በአፍሪካ የሚገኙ ከፍተኛ ባለስልጣናት እና የዓለም አቀፍ ድርጅቶችና ባለሃብቶች እየተሳተፉ መሆኑን ከጽህፈት ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የአፍሪካ ኢንቨስትመንት ፎረሙ ነገ ይጠናቀቃል።