አልባሳር ኢንተርናሽናል ፋውንዴሽን በአዲስ አበባ እና አክሱም ከተሞች ነፃ የአይን ህክምና ሊሰጥ ነው

719

አዲስ አበባ ጥቅምት 29/2011 “አልባሳር ኢንተርናሽናል ፋውንዴሽን” የተሰኘው የሳኡዲ አረቢያ ግብረ ሰናይ ድርጅት የህክምና ቡድን በኢትዮጵያ ነጻ የዓይን ህክምና ለመስጠት ነገ አዲስ አበባ ይገባል።

ቡድኑ በኢትዮጵያ ቆይታው በአዲስ አበባና ትግራይ ክልል አክሱም ከተማ ለሚገኙ ከ10 ሺህ በላይ ለሚሆን ህዝብ የዓይን ምርመራና ህክምና እንደሚሰጥ የፋውንዴሽኑ ዋና ሥራ አስፈፃሚ መምህር ያሲን ራጁኡ ዛሬ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ገልፀዋል።

በተለያዩ የዓለም ክፍሎች 29 ሆስፒታሎችና አራት የዓይን ህክምና ማሰልጠኛ ተቋማትን ገንብቶ ለአገልግሎት እንዳበቃ የሚነገርለት ፋውንዴሽኑ በኢትዮጵያም ካለፉት 13 ዓመታት ጀምሮ የዓይን ህክምና እየሰጠ ይገኛል።

ካለፉ 18 ዓመታት ጀምሮ በጋምቤላ፣ ድሬደዋ፣ አሶሳ፣ ማይጨውና ሌሎች 29 የኢትዮጵያ ከተሞች 148 ሺ ለሚጠጉ ሰዎች የዓይን ህክምና አገልግሎት ሰጥቷል፤ ከ20 ሺህ ለሚልቁት ደግሞ የዓይን ቀዶ ህክምና አከናውኗል።

ዋና ሥራ አስፈፃሚው እንዳሉት ነገ አዲሰ አበባ የሚገባው የህክምና ቡድን 18 አባላትን የያዘ ሲሆን  ህዳር 2 እና 3 ቀን 2011 ዓም በአክሱም ቅድስት ማርያም ሆስፒታል በመገኘት በአክሱምና አካባቢው ለሚገኙ የዓይን ህሙማን ነፃ ምርመራና ህክምና ይሰጣል። 

ከህዳር 8 ቀን 2011 ዓም ጀምሮ ባሉት ዘጠኝ ቀናት ደግሞ በአዲስ አበባ ከተማ አለርት ሆስፒታል በተመሳሳይ ነፃ የአይን ምርመራ፣ የአይን ሞራ ገፈፋ፣ የመነፅርና የመድሀኒት አቅርቦትን ጨምሮ ዘርፈ በዙ የዓይን ህክምና አገልግሎት እንደሚሰጥ ዋና ሥራ አስፈፃሚው ተናግረዋል።

የህክምና ቡድኑ በመቄዶንያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል በመገኘትም ተመሳሳይ አገልግሎት ይሰጣልም ተብሏል።

የቀዶ ህክምና ለሚያስፈልጋቸው የማእከሉ ህሙማን ደግሞ በአለርት ሆስፒታል ህክምናው እንደሚደረግ አስረድተዋል።

ዋና ሥራ አስፈፃሚው እንዳሉት በአክሱምም ሆነ በአዲስ አበባ በተጠቀሱት ቀናት በየሆስፒታሎቹ በመገኘት ህክምናውን ማግኘት ይችላሉ ተብሏል።

በተለይ አቅመ ደካሞችና ህይወታቸውን በዝቅተኛ ገቢ የሚመሩ ዜጎች የእድሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ዋና ሥራ አስፈፃሚው ጥሪ አቅርበዋል።

የአለርት ሆስፒታል የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ አለምሰገድ ጫኔ በበኩላቸው ሆስፒታሉ የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን ማጠናቀቁንና የሆስፒታሉ ባለሙያዎች የህክምና ቡድኑን ለማገዝ ዝግጁ መሆናቸውን ገልፀዋል።

ህክምናውን ማግኘት የሚፈልጉ ሰዎች በእለቱ በመመዝገብ ጭምር ህክምናውን ማግኘት እንደሚችሉም ተናግረዋል።

በተያያዘ ዜና አልባሳር ኢንተርናሽናል ፋውንዴሽን ከነፃ ህክምናው በተጨማሪ በኢትዮጵያ የዓይን ህክምና ሆስፒታሎችንና ማሰልጠኛ ማዕከል ለመገንባት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን መምህር ያሲን አስረድተዋል።

ፋውንዴሽኑ አራት  ቢሊዮን ብር ወጪ በማድረገ  በ9ኙ የአገሪቱ የክልል መንግስታትና ሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች 11 የዓይን ህክምና  ሆስፒታሎችን ለመገንባት አቅዷል።

በዚህም መሰረት በአዲስ አበባ ግንባታውን ለማካሄድ የሚያስፈልገውን 10 ሺህ ካሬ ሜትር ቦታ ማግኘቱን ነው መምህር ያሲን የገለፁት።

ፋውንዴሽኑ ላለፉት 29 ዓመታት በ45 የዓለም አገራት የዓይን ክህምና አገልግሎት በመስጠት ላይ መሆኑ ተመልክቷል።

በዚህም 40 ሺ የሚጠጋ የዓይን መነፅርና ሌሎች የምክርና የመድሃኒት አቅርቦት አገልግሎትን ሰጥቷል።