እየጣለ ያለው ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በሰብል ላይ ጉዳት እንዳያደርስ አርሶ አደሩ ፈጥኖ ምርቱን እንዲሰበስብ ተጠየቀ

145
አዲስ አበባ ጥቅምት 29/2011 በኢትዮጵያ አንዳንድ አካባቢዎች የሚጠበቀው ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በደረሱ ሰብሎች ላይ ጉዳት እንዳያደርስ አርሶ አደሩ ፈጥኖ ምርቱን እንዲሰበስብ ጥሪ ቀረበ። የመከላከያ ሰራዊት አባላትንና ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ የተለያዩ አካላት ምርት በመሰብሰብ ሂደቱ አቅመ ደካሞችንና ከፍተኛ ምርት ያለባቸው አካባቢዎች አርሶ አደሮችን እንዲደግፉም ጥሪ ቀርቧል። የግብርና ሚኒስቴርና ብሔራዊ የሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ በአንዳንድ የአገሪቱ ክፍሎች እየጣለ ያለውን ያልተጠበቀ የዝናብ ሁኔታና ሊወሰድ በሚገባው ጥንቃቄ ዙሪያ በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል። የብሔራዊ የሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር አቶ ፈጠነ ተሾመ በዚሁ ወቅት እንደገለፁት በተፈጠረው የኢሊኖ አየር መዛባት ሳቢያ በኢትዮጵያ ሰሜናዊ አጋማሽ ክፍል ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ መጣል ጀምሯል። ከቀላል አስከ ከባድ መጠን ያለው ይኸው ወቅታዊ ያልሆነ ዝናብ በትግራይ፣ አማራ፣ በምዕራብ ኦሮሚያና ጋምቤላ ክልሎች እየዘነበ ሲሆን ለመጪዎቹ አስር ቀናትም እንደሚቀጥል ገልፀዋል። በመሆኑም አርሶ አደሩ የደረሱ ሰብሎቹን ከጥፋት እንዲከላከል የግብርና ሚኒስቴር ጥሪ አቅርቧል። የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ሳኒ ረዲ እንደገለፁት ወቅቱን ያልጠበቀው ዝናብ ጉዳት እንዳያደርስ ገበሬው ጊዜ ሳይሰጥ ፈጥኖ በመረባረብ የደረሱ ሰብሎችን መሰብሰብ አለበት። ምርቱን ፈጥኖ ማንሳት ካልተቻለ በአጠቃላይ የአገሪቱ ምርት መጠንና ጥራት ላይ ተፅእኖ እንደሚያሳድርም አቶ ሳኒ ተናግርዋል። ትምህርት ቤቶች፣ ከፍተኛ የትምህርት ተቃማትና የመከላከያ ሰራዊት አባላት በሚገኙበት አካባቢ አቅመ ደካሞችና ከፍተኛ ምርት ያለባቸው አርሶ አደሮችን እንዲደግፉም ጥሪ አቅርበዋል። አርሶ አደሩ ከማሳ እስከ ጎተራ ባለው የምርት መሰብሰብ ሂደት የምርት ብክነት እንዳያጋጥም ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲደረግም ሚኒስቴር ዲኤታው አሳስበዋል። ከዚህም በተጨማሪ ኮምባይነርን ጨምሮ የምርት መሰብሰቢያና መውቂያ ቴክኖሎጂ ያላቸው ድርጅቶች፣ ባለሀብቶችና ተቋማት በተመጣጣኝ ዋጋ ምርቱን በመሰብሰብ ሂደት ገበሬውን ለመደገፍ እንዲዘጋጁ መደረጉን አቶ ሳኒ ተናግረዋል። የደረሱ ሰብሎችን የመሰብሰብ ሂደቱ እየተከናወነ መሆኑን የገለፁት አቶ ሳኒ አስካሁንም በአገሪቱ ካለው የሰሊጥ ማሳ 75 በመቶ ያህሉ ተሰብስቧል ነው ያሉት። ወቅቱን ያልጠበቀውን ዝናብ ጥቅም ላይ ለማዋል ገበሬው ምርቱን እንደሰበሰበ ወዲያውኑ የማሳው እርጥበት ሳያልቅ የመጀመሪያው የእርሻ ሥራ እንዲያከናውን መልዕክት አስተላልፈዋል። ወቅቱን ያልጠበቀው ዝናብ ዘግይቶ ለተዘሩ ሰብሎች፣ ሁለተኛ ዝናብ ወቅታቸው ለሆኑ የደቡብና ደቡብ ምስራቅ አካባቢዎችና  ቀጣይ የእርሻ ሥራን አጠናክሮ ለመቀጠልና ለእንስሳት የመጠጥና የመኖ ልማት ምቹ ሁኔታ ይፈጥሯል ተብሏል። በአፋር፣ በደቡብና ደቡብ ምስራቅና ሌሎች አካባቢዎች  የአሜሪካ መጤ ተምችን ጨምሮ የሰብል ተባዮችን ለመከላከል አርሶ አደሩ ሳይዘናጋ በየጊዜው ማሳውን የመቃኘት ሥራ እንዲያከናውንም አስገንዝበዋል። ከዚህ በተጨማሪ ዝናቡ በሱማሌ ክልል ለአንበጣ መራቢያ ምቹ ሁኔታ ሊፈጠር ስለሚችል ወቅቱን የጠበቀ አሰሳ እንዲደረግም ማሳሰቢያ ተሰጥቷል። በየአካባቢው የሚገኙ የግብርና ባለሙያዎችና የመንግስት አመራሮች ከገበሬው ጋር በመተባበር ምርት በመሰብሰብ ሂደቱን የማቀላጠፍና የመደገፍ ሚናቸውን እንዲወጡ የግብርና ሚኒስቴር አሳስቧል። ዘንድሮ በመላው ኢትዮጵያ በሰብል ከተሸፈነው 14 ሚሊዮን ሄክታር፤ 375 ሚሊዮን ኩንታል እህል ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም