የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ እያሽቆለቆለ ነው

66
አዲስ አበባ ጥቅምት 29/2011 ካለፉት አራት ዓመታት ጀምሮ የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ አፈጻጸም ከማደግ ይልቅ እያሽቆለቆለ ይገኛል። የዓለም ገበያ ዋጋ መቀዛቀዝ፣ የግብርና ምርቶች በብዛትና በጥራት አለመቅረብ፣ የመሰረተ-ልማት አቅርቦት አለመሟላትና የኮንትሮባንድ ንግድ የወጪ ንግዱ ቅናሽ ማሳየት ከጀመረባቸው ዓመታት ጀምሮ ሲጠቀሱ የነበሩ ዋና ዋና ችግሮች ናቸው። እነዚህ ችግሮች ቀድመው የተለዩ ቢሆንም እስካሁን መፍትሄ ባለማግኘታቸው የወጪ ንግዱ አፈጻጸም ከዓመት ዓመት ቅናሽ ማሳየቱን አላቆመም። በ2011 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት እንኳን የወጪ ንግዱ አፈጻጸም ከአምና ተመሳሳይ ወቅት ከነበረው ጋር ሲነጻጸር በሰባት ነጥብ 43 በመቶ ቀንሷል። በሩብ ዓመቱ 889 ነጥብ 69 የአሜሪካ ዶላር ለማግኘት የታቀደ ቢሆንም ማግኘት የተቻለው ከ628 የአሜሪካን ዶላር ያልዘለለ ነው። በተለይ የማዕድን ዘርፉ ከሌሎች ዘርፎች የበለጠ ዝቅተኛ አፈጻጸም አሳይቷል። በሩብ ዓመቱ ከዘርፉ ለማግኘት የታቀደው 82 ነጥብ 86 የአሜሪካ ዶላር የነበረ ሲሆን የተገኘው ግን 18 ነጥብ 89 ሚሊዮን ዶላር ወይም የዕቅዱን 22 ነጥብ 7 በመቶ ብቻ ነው። ይህም አምና በተመሳሳይ ወቅት ከነበረው አፈጻጸም የ44 በመቶ ቅናሽ አለው። ለዚህ  ዝቅተኛ አፈጻጸም መገኘት እንደ ምክንያት የተቀመጠው ማዕድን በሚመረትበት አካባቢ ተከስቶ በነበረው የጸጥታ ችግር አምራቾች ተረጋግተው ባለማምረታቸው ለብሄራዊ ባንክ የሚገባው ወርቅ መጠን ቅናሽ ማሳየቱ ነው። የኮንትሮባንድ መስፋፋትና የባለድርሻ አካላት የቅንጅት ክፍተትና የሎጂስቲክ አለመሟላት ሌሎች ተግዳሮቶች ናቸው ተብሏል። ለመሆኑ በየዓመቱ ቁልቁል እየሄደ ያለውን የወጪ ንግድ ለማሳደግ ምን አይነት መፍትሄ ያስፈልጋል። የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎቹ ምክረ ሀሳባቸውን ያስቀምጣሉ። ዶክተር አሰፋ አድማሴ የገበያ አማራጮችን ማየት ፣ ኤክስፖርትን ማበረታታት ፣የውጭ ምንዛሬ ማግኛ መንገዳችን በማስፋት  የውጭ ንግድ ከፍተኛ አስተዋጽ እንዳለው አስረድተዋል፡፡ ''አላስፈላጊ ነገሮችን ለጊዜው ባናስመጣ ምን እንሆናለን ምንም አንሆንም የ8 የ9 ሚሊዮን ብር መኪናዎች ኢትየጵያ ውስጥ ኢምፖርት የሚደረገው ለምንድነው ብለን መጠየቅ አለብን” የሚሉት አቶ ዘመዴነህ ንጋቱ የውጭ ምንዛሬን በአግባቡ መጠቀም አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የወጪ ንግድ ዳይሬክተር ጄኔራል አቶ አሰፋ ሙሉጌታ በወጪ ንግዱ አፈጻጸም ላይ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮች የተለመዱ መሆናቸውን ያረጋግጣሉ። በሩብ ዓመቱ ከግብርና ምርቶች 604 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ለማግኘት ታቅዶ 628 የአሜሪካ ዶላር ተገኝቷል። ከማምረቻ ኢንዱስትሪው 180 የአሜሪካ ዶላር ለማግኘት ታቅዶ 119 ብቻ ተገኝቷል። በተመሳሳይ ከኤሌክትሪክና ሌሎች ምረቶች 21 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ለማግኘት ታቅዶ የተፈጸመው 19 ብቻ ነው። ወደ ውጭ የሚላኩ የግብርና ምርቶችን ስብጥር ማሳደግና ምርቶቹ ላይ እሴት መጨመር እንዲሁም የኢንዱስትሪ ምርቶችን በብዛትና በጥራት ማምረት ሌላው መፍትሄ ነው ብለዋል። የግብርና ምርቶች በሚፈለገው መጠንና ጥራት አለመቅረብ፣ በቡናና አንዳንድ የጥራጥሬዎች ምርቶች ላይ የዓለም ገበያው ዋጋ መቀነሱ፣ በአንዳንድ የቅመማ ቅመም ምርቶች ላይ የአፍላቶክሲን መከሰትና የገዥዎች የመግዛት ፍላጎት መቀነስ በምክንያትነት ተጠቅሰዋል። የወጪ ንግድ ምርቶቹ በ123 መዳረሻ አገራት የተላኩ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ ሶማሊያ፣ አሜሪካ፣ ኔዘርላንድስ፣ ቻይና እና ሳኡዲ አረቢያ በቅደም ተከተል ከፍተኛውን ገቢ ካስገኙ 10 አገሮች ውስጥ ከአንድ እስከ አምስት ተቀምጠዋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም