በምስራቅ ሐረርጌ ዞን ግራዋ ወረዳ 40 የሣር ክዳን ቤቶች በእሳት ተቃጠሉ

94
ሐረር ጥቅምት 29/2011 በምስራቅ ሐረርጌ ዞን ግራዋ ወረዳ ሙዲና ጅሩ በሊና ቀበሌ ገበሬ ማህበር 40 የሣር ክዳን ቤቶች ባልታወቀ ምክንያት በእሳት መቃጠላቸውን የዞኑ ፖሊስ መምሪያ ገለጸ። የመምሪያው የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ዲቪዥን ኃላፊ ኮማንደር ስዩም ደገፋ ዛሬ ለኢዜአ እንደገለጹት በቀበሌው ከጥቅምት 25 እስከ 28 ቀን 2011ዓ.ም ተቃጠሉ የተባሉት የሳር ክዳን በቶች ህብረተሰቡ "ከሰማይ በዘነበ እሳት ነው" ቢሊም ፖሊስ ማስረጃ አላገኘም። በአሁኑ ወቅትም የወረዳው ፖሊሶች የአደጋ መንስዔ  ምን እንደሆነ በማጣራት ላይ ናቸው ብለዋል። ከስድስት ዓመት በፊት ቤቶቹ ተቃጥለዋል በተባለበት ሥፍራ የሚገኝ ሌላ አንድ አካባቢ ላይ ተመሳሳይ ችግር ተከስቶ እንደነበር ያስታወሱት ኮማንደር ስዩም በወቅቱ የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ምሁራንና ፖሊስ የክስተቱን መንስኤ ለማወቅ ጥረት ማድረጋቸው አስታውሰዋል። በወቅቱ ምንም ምላሽ ሳይገኝ እሳቱ መጥፋቱን ገልጸው በአሁኑ ወቅትም ተመሳሳይ ድርጊት ስለመከሰቱ ከህብረተሰቡ መረጃ መምጣቱን ገልጸዋል። አሁንም ፖሊስ ከሚያከናውነው የማጣራት ሥራ ጎን ለጎን የዘርፉን ሞያተኞች ወደ ሥፍራው በመላክ የማጣራት ሥራ እንደሚከናወን ኮማንደር ስዩም ተናግረዋል። ደረሰ በተባለው የእሳት አደጋ ቤቶቹ ቢቃጠሉም በሰው ሕይወትና አካል ላይ ጉዳት አለመድረሱን ኮማንደር ስዩም አክለው ገልጸዋል። የኢዜአ ሪፖርተር በግራዋ ወረዳ ጋራ ሙለታ ከተማ በስልክ ያነጋገራቸው አንድ ነዋሪ ክስተቱን በአካል ተገኝተው ባይመለከቱም ቃጠሎ ወደተከሰተበት አካባቢ ሰዎች ሄደው እየተመለከቱ ስለመሆኑ ገልፀዋል። ከእዚህ በተጨማሪ በአካባቢው ቤታቸው ያልተቃጠለባቸው ነዋሪዎች ተመሳሳይ ክስተት ይከሰታል በሚል ከቤት ወጥተው ሜዳ ላይ መቀመጣቸውን የገለጹበት ሁኔታ መኖሩን አረጋግጧል ።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም