የትራንስፖርት ሚኒስቴር በአዲስ አበባ ያሉ ባቡሮች በሙሉ አቅም አገልግሎት እንዲሰጡ ድጋፍ እንደሚደረግ ገለጸ

1759

አዲስ አበባ ጥቅምት 29/2011 የአዲስ አበባ ቀላል የባቡር ትራንዚት ፕሮጀክት ያሉ ባቡሮች በሙሉ አቅም ለህብረተሰቡ አገልግሎት እንዲሰጡ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ የትራንስፖርት ሚኒስቴር ገለጸ።

የትራንስፖርት ሚኒስትር ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ፕሮጀክት ዋና መስሪያ ቤት የቃሊቲ ዴፖ የስራ እንቅስቃሴን  ጎብኝተዋል።

ሚኒስትሯ በዴፖት ያለውን የኦፕሬሽንና ጥገና፣ የባቡር ደህንነትና ፀጥታ ቁጥጥር የሚደረግበትንና ባቡሮች የሚያድሩበትን የስራ ክፍሎችን የተመለከቱ ሲሆን ከጉብኝቱ በኋላም ከአገልግሎቱ የስራ ሃላፊዎች ጋር ተወያይተዋል።

ጉብኝቱ የአዲስ አበባ ቀላል የባቡር ትራንዚት ፕሮጀክት አገልግሎት ዙሪያ ያሉት መልካም አጋጣሚዎችና ፈተናዎችን ለማወቅ ማለሙን  ገልጸዋል።

 ባቡሮች በሙሉ አቅም ለህብረተሰቡ አገልግሎት እንዳይሰጡ ዋነኛ እንቅፋት የሆነውን የመለዋወጫ እቃና የውጭ ምንዛሬ ችግር ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር ለመፍታት ሚኒስቴሩ እንደሚሰራ ወይዘሮ ዳግማዊት ተናግረዋል።

 በሃይል አቅርቦት ረገድም ያለውን ችግር ለመፍታት ከኢትዮጵያ ኤሌትሪክ አገልግሎት ጋር በመነጋገር ችግሩን ለመፍታት እንደሚሰራና ለዚህም አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ጠቅሰዋል።

 በትራንስፖርት ሚኒስቴር የ100 ቀናት እቅድ ውስጥ አንድ የባቡር ተሳፋሪ በባቡር ጣቢያ ባቡር ለማግኘት የሚጠብቅበትን የ15 ደቂቃ ጊዜ ወደ 12 ደቂቃ ዝቅ ለማድረግ ጥረት እንደሚደረግ ተናግረዋል።

የፕሮጀክቱን አብዛኛውን ስራ ኢትዮጵያውያን ዜጎች ተረክበው መስራት መጀመራቸው መልካም ጅምር እንደሆነና በአጠቃላይ ፕሮጀክቱ ለባቡር ትራንስፖርት እድገት መሰረት የሚጥል እንደሆነም ነው ወይዘሮ ዳግማዊት ያስረዱት።

መንግስት የባቡርን በአጠቃላይ በትራንስፖርቱ ዘርፍ ዘመናዊና ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት እርካታ እንዲያገኝ ትኩረት ሰጥቶ በስፋት እንደሚንቀሳቀስ አመልክተዋል።

በአዲስ አበባ ቀላል የባቡር ትራንዚት ፕሮጀክት ለተሳፋሪዎች የሚያገለግሉ 41 ባቡሮች ቢኖሬትም በአገልግሎት አሰጣጣቸው በህብረተሰቡ ቅሬታ ሲነሳባቸው ይስተዋላል።

በኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሄኖክ ቦጋለ እንደገለጹት፤ በአሁኑ ሰአት የተሸለ አገልግሎት መስጠት የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሆነ ገልጸዋል።

ኮርፖሬሽኑ በ100 ቀናት እቅድ ውስጥ አገልግሎት የሚሰጡ ባቡሮችን ቁጥር በመጨመር የህብረተሰብ እርካታ ለማሳደግ ተሰልፎ የሚቆየውን ህብረተሰብ እንዳይጉላላ ተጠቀሚነቱን ለማስፋት እየተሰራ እንደሆነ ተናግረዋል።

ባቡሮች በሙሉ አቅማቸው አገልግሎት እንዳይሰጡ ከሚያደርጉ ዋንኛ ምክንያቶች አንዱ ባቡሮች ሲበላሹ ቻይና ወስዶ ጥገና ለማድረግ የሚወስደው ጊዜ እንደሆነ አመልክተዋል።

ይህንንም ችግር ለመፍታት ከቻይና መንግስት ጋር በመነጋገር የባቡር ጥገና ማዕከል ግንባታ ለመገንባታ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን ነው አቶ ሄኖክ ያስረዱት።

በትኬት አቆራረጥ ላይ ያለውን ችግር ለመፍታት ዘመናዊ የትኬት ስርአት ለመጀመር ጥረት እያደረገ መሆኑንና በባቡር መስመሮች ላይ የሚደርሰውን አደጋ ለመቀነስ የተቀናጀ የአደጋ መከላከል ግብረ ሃይል ተቋቁሙ በቅርቡ ስራ እንደሚጀምር ጠቁመዋል።

 የሃይል አቅርቦት መቆራረጥ፣ የሚገኘው ገቢና ወጪ አለመጣጠን፣ የመለዋወጫ እቃዎች በበቂ ሁኔታ አለመገኘትና ለዕቃዎች ግዢ በቂ የውጭ ምንዛሬ ገንዘብ አለማግኘት የአገልግሎቱ ዋነኛ ተግዳሮቶች እንደሆኑና መንግስትም ጉዳዩን አይቶ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

 34 ኪሎ ሜትር  ርዝመት ያለው የአዲስ አበባ ቀላል የባቡር ትራንዚት ፕሮጀክት ተጠናቆ መንገደኞችን ማመላለስ የጀመረው በመስከረም 10 ቀን 2008 ዓ.ም ነው።

የባቡር መሰረተ ልማት ያለውን ስትራቴጂያዊ ጥቅም በመገንዘብ በትራንስፖርት ሚኒስቴር ስር የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን በ2000 ዓ.ም ተቋቁሞ አገልግሎት መስጠት መጀመሩን ከኮርፖሬሽኑ የተገኘ መረጃ ያመለክታል።