የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤትን በአዲስ መልክ ለማደራጀት የሚያስችል ረቂቅ ህግ ተዘጋጀ

203
አዲሰ አበባ ጥቅምት 29/2011 የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤትን በአዲስ መልክ ለማደራጀት የሚያስችል ህግ ማርቀቁን በቅርቡ የተቋቋመው የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ተቋማዊ ለውጥ የጋራ ኮሚቴ አስታወቀ። ህግ ከማርቀቅ ባሻገር የተለያዩ የአሰራር ስርዓቶችን ለመዘርጋት የሚያስችሉ ሰነዶችንም አዘጋጅቷል። በተዘጋጀው ህግና ሌሎች አዳዲስ የአሰራር ደንቦች ላይ ህዝበ ሙስሊሙ እንዲመክር ይደረጋልም ተብሏል። የህዝበ ሙስሊሙ መሪ ተቋም አሰራርን ጨምሮ በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ በኢትዮጵያዊያን ህዝበ ሙስሊምና ሊቃውንቱ መካከል ለረጅም ዓመታት የቆየ ልዩነት አለ። ይህ ወደ ግጭት ጭምር እያመራ የነበረውን አለመግባባት በመግታት አንድነትን ለማምጣት በተለያየ ጎራ ተሰልፈው በነበሩት አካላት መካከል ከጥቂት ወራት በፊት እርቀ ሰላም ወርዷል። በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ አነሳሽነት የተፈጠረውን ይህን እርቀ ሰላም ተከትሎ ነበር የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ተቋማዊ ለውጥ የጋራ ኮሚቴ የተቋቋመው። ኮሚቴው በተለይ በሙስሊሙ መሪዎችና ሊቃውንቱ መካከል የነበረውን ልዩነት በማስወገድ አጠቃላይ የሙስሊሙ መሪ ድርጅትና አሰራር ለአገርና ህዝበ ሙስሊሙ የጋራ ጥቅም የሚበጅ የሚሆንበትን መንገድ መቀየስ ዋነኛ ግቡ ነበር። ኮሚቴው ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ባከናወናቸው በእነዚህ ተግባራት እና አጋጥመውኛል ባላቸው ችግሮች ላይ በማተኮር ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል። የኮሚቴው ቃል-አቀባይ ኡስታዝ ካሚል ሸምሱ በዚሁ ወቅት "ኮሚቴው የሚሰራው በኢስላማዊው ተቋም ዘንድ ለሚታዩት ችግሮች ጊዜያዊ መፍትሄ ለመስጠት ብቻ አይደለም፤ ይልቁንም ተቋሙ ለትውልድ የሚሸጋገር፣ ሁሉን አቀፍና ጠንካራ የሚሆንበትን ወጥ የሆነ አሰራር ለመዘርጋት ተግቶ በመስራት ላይ ነው" ብለዋል። ይህንንም እውን ለማድረግ በዘርፉ በቂ እውቀትና ልምድ ያካበቱ ምሁራን የተካተቱባቸው የመዋቅር ጥናት፣ የኢስላማዊ ሊቃውንት መግባቢያ ሰነድ፣ የኃብት አፈላላጊና የህግ ጉዳዮች ንኡስ ኮሚቴዎች ተዋቅረው የተለያዩ ተግባራት መከናወናቸውን አመልክተዋል። በተለይም 14 የህግ ባለሙያዎች የተሳተፉበት የህግ ነክ ጉዳዮች ንዑስ ኮሚቴ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት አስተማማኝ መሰረት ኖሮት ህጋዊ እውቅና እንዲያገኝ ለማድረግ የሚያስችለውን ረቂቅ ሰነድ አሰናድቶ ለዋናው ኮሚቴ መርቷል። የመዋቅር ጥናት ንኡስ ኮሚቴ በበኩሉ የእስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤቶች አወቃቀርን መልሶ ለማደራጀት የሚያስችል ጥናት ማካሄዱን ቃል አቀባዩ ተናግረዋል። ጥናቱ የምክር ቤቶች አባላት የምርጫ ሂደት የሚመራበትን ሰነድ ማዘጋጀቱን ነው ቃል-አቀባዩ ጨምረው ያመለከቱት። አዲሱ አደረጃጀት እስከ መስጂዶች አስተዳደር ድረስ የሚወርድ መሆኑም አክለዋል። ኡስታዝ ካሚል እንዳሉት ከአገሪቱ የአስልምና አስተምህሮ ጋር በተያያዘ በእምነቱ ሊቃውንት መካከል የቆየውን አለመግባባትና ግጭት ለማስወገድ የሚያግዝ የመፍትሄ አቅጣጫን የሚያመላክት አሰራርም ይዘረጋል። በዚህም መሰረት የአገሪቱን የእስልምና ሃይማኖት አስተምሮን የሚገዛ፣ የእምነቱ ሊቃውንትም የሚመሩበትና ''የኡለማዎች መግባቢያ'' የሚሰኝ ሰነድ ተዘጋጅቶ ምክክር እየተደረገበት ነው። ኡስታዝ ካሚል አክለውም የኢትዮጵያ ሙስሊሞችን የሚመራው ተቋም አደረጃጀትና አሰራር የተዋጣለት ይሆን ዘንድ የተለያዩ የውጭ አገራትን ልምድ ለመቅሰም ጥረት  ተደርጓል ብለዋል። ከዚህም ባሻገር ኮሚቴው በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች በተለይ ከመስጂድ አስተዳደር ጋር ተያየዞ የሚከሰቱ ችግሮችን ለመፍታት ጥረት እያደረገ መሆኑም ተመልክቷል። ኮሚቴው ይህን ስራ በሚከውንበት ወቅትም የተለያዩ ችግሮች እንደገጠሙትም ጠቅሰዋል። ከነዚህም መካከል ሰሞኑን የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ምክር ቤት በፕሬዝዳንቱ ሼህ ሙሃመድ ሸሪፍ ላይ ያስተላለፈው የስራ እገዳ አንዱ መሆኑን ተናግረዋል። "ኮሚቴው አገራዊ አንድነትና ትውልዱ ጭምር የሚመራበትን ተቋምና አሰራር ለማምጣት በሚጥርበት በዚህ ወቅት ይህ ውሳኔ መተላለፉ አግባብ አይደለም" ብለዋል። ውሳኔው ወቅቱን ያላገናዘበና በተገቢው ግምገማ ላይ ያልተመሰረተ ከመሆኑም በላይ ኮሚቴው እያካሄደ ካለው የእርቅና የአንድነት ግንባታ ጉዞ ጋር የሚጣረስ በመሆኑ የተወገዘ ነው" ሲሉም ገልፀዋል። በመሆኑም የሚመለከታቸው የፌዴራልና የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤቶች በጉዳዩ ላይ እንዲያስቡበት መክረዋል። ከዚህም ሌላ የኮሚቴውን ስምና ተግባር ለማጠልሸት የሚሰራጩ የሀሰት መረጃዎች መኖራቸውን ያመለከቱት ኡስታዘ ሸምሱ "ኮሚቴው ለአንድ ወገን የቆመ ነው፤ የመውሊድ በዓል እንዳይከበር ከልክሏል፤ በሚል የሚሰራጨው መረጃ ከእውነት የራቀና ህዝብን ለጥፋት የሚያነሳሳ ነው" ሲሉ ኮንነዋል። በመግለጫ የተሳተፉ የኮሚቴው ሰብሳቢ ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጅ ኡመር እድሪስ በበኩላቸው ሁሉም ለአገራዊ ሰላምና አንድነት በጋራ እንዲተጋ አሳስበዋል። ህዝበ ሙስሊሙ በአሁኑ ወቅት የጋራው በሆኑት መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ ከተስማማ ዝርዝር ጉዳዮችን ለሚወክለው አዋቂዎችና ኡለማዎች መተው እንደሚጠበቅበትም መክረዋል። ከመጪው የህዳር ወር ጀምሮ ህጎቹና አዳድሶቹ መዋቅሮች ዙሪያ ህዝባዊ ውይይቶች እንደሚካሄዱም ተገልጿል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም