አንድነታችንን በማጠናከርና እርስ በእርስ በመደጋገፍ ብቁ ዜጋ ለመሆን እንሰራለን-የመቱ ዩኒቨርሲቱ አዲስ ገቢ ተማሪዎች

50
መቱ ጥቅምት 29/2/2011 በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው አንድነታቸውን በማጠናከርና እርስ በእርስ በመደጋገፍ ብቁ ዜጋ ሆነው ለመውጣት እንደሚሰሩ በመቱ ዩኒቨርሲቱ የተመደቡ አዲስ ገቢ ተማሪዎች ገለጹ፡፡ ዩኒቨርሲቲው የተመደቡለትን 2 ሺህ 72 አዳዲስ ገቢ ተማሪዎች ትናንት ተቀብሏል፡፡ በዩኒቨርሲቲው በተዘጋጀ የአቀባበል ስነስርአት ላይ ተማሪዎቹ እንዳሉት በመካከላቸው ያለውን አንድነትና ፍቅር ለማጠናከርና ሰላማዊ የመማር ማስተማር አካባቢ ለመፍጠር የበኩላቸውን እገዛ ያደርጋሉ፡፡ ከአማራ ክልል ወረታ የመጣችው ተማሪ አማረች አንዱአለም በሰጠችው አስተያየት በዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብና በነባር ተማሪዎች የተደረገላት አቀባበል ያልገመተችውና የተለየ ስሜት እንደፈጠረባት ተናግራለች፡፡ “በተቋሙ ቆይታዬ ከሌሎች ተማሪዎች ጋር መልካም ግንኙነት በመመስረትና እርስ በርስ በመረዳዳት የመጣሁበትን አላማ ለማሳካት እጥራለው” ብላለች፡፡ ጊዜውን በአግባቡ በመጠቀም በትምህርቱ ውጤታማ ለመሆን ማቀዱን የተናገረው ደግሞ ከሆሳዕና ከተማ እንደመጣ የተናገረው ተማሪ አያሌው ከበደ ነው፡፡ " ከቤት ስነሳ በትምህርቴ የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ አቅጄ ነው የመጣሁት " ያለው ተማሪው በዩኒቨርሲቲው ሰላማዊና ምቹ የትምህርት አካባቢ ለመፍጠር በሚደረገው ጥረት የበኩሉን ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን ተናግሯል፡፡ በዩኒቨርሲቲው ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች ከመጡ ተማሪዎች ጋር እርስ በርስ በመደጋገፍ አንድነቱን ለማጠናከር እንደሚሰራም ገልጿል ከጋምቤላ ክልል ማጃንግ ዞን የመጣችው ኦቻር ኡጁሉ በበኩሏ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም የተለያዩ ባህል፣ ቋንቋና ማንነቶች ያሏቸው ተማሪዎች የሚገኙበት መሆኑ እርስ በርስ ለመተዋወቅ የተሻለ እድል እንደሚፈጥርላት ተናግራለች፡፡ "በቂ እውቀት ይዞ ለመውጣትና እርስ በእርስ ለመቀራረብ ሰላማዊ የትምህርት አካባቢ መፍጠር አስፈላጊ ነው" ያለችው ወጣቷ በዚህ በኩል የሚጠበቅባትን ለመወጣት ዝግጁ መሆኗን ተናግራለች፡፡ የመቱ ዩኒቨርሲቲ የህዝብና ውጪ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ኦልቀባ አሰፋ እንዳሉት ዩኒቨርሲቲው ተማሪዎቹን በአግባቡ ለማስተናገድና የተሟላ አገልግሎት ለመስጠት የተማሪ ተወካዮች በተሳተፉበት አስፈላጊ ዝግጅት ሲያደርግ ቆይቷል። ካለፈው ክረምት ጀምሮ በተከናወኑ የዝግጅት ሥራዎች ከምግብ ቤት፣ ከመኝታ አገልግሎትና ከንጹህ ውሃ አቅርቦት ጋር በተያያዘ ሲነሱ የነበሩ ቅሬታዎችን ሙሉ ለሙሉ ለመፍታት መቻሉንም ተናግረዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በዘንድሮው የትምህርት ዘመን በመቱ ዋና ግቢና በበደሌ ካምፓስ 2ሺህ 72 አዲስ ተማሪዎችን መቀበሉንም አስረድተዋል፡፡ የመቱ ዩኒቨርሲቲ በአሁኑ ወቅት በመቱና በደሌ ካምፓሶች በ41 የትምህርት ክፍሎች ዘንድሮ የተመደቡለትን ጨምሮ ከ7 ሺህ 670 በላይ ተማሪዎችን ተቀብሎ በመደበኛው መርሀግብር እንደሚያስተምር ታውቋል፡፡    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም