እምቦጭን ከአባያ ሐይቅ ለማስወገድ በቂ ጥናት እንደሚያስፈልግ ተገለጸ

1073

አርባምንጭ/ሃዋሳ ጥቅምት 29/2011 የእምቦጭ አረምን ከአባያ ሐይቅ ማስወገድ ከመጀመሩ በፊት በቂ ጥናት እንደሚያስፈልግ የጋሞ ጎፋ ዞን ደንና አከባቢ ጥበቃ ጽህፈት ቤት ገለጸ።

የጽህፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ዮሰፍ ኩማ ለኢዜአ እንዳሉት ሐይቁ በውስጡ አዞን ጨምሮ የተለያዩ ተሳቢ እንስሳት በመያዙ አረሙን በሰው ጉልበት ለማስወገድ የተደረገው ሙከራ አልተሳካም።

መስሪያ ቤታቸው ባለፈው ዓመት በካሄደው የዳሰሳ ጥናት ከ1 ሺህ 705 ሄክታር በላይ የሐይቁ ክፍል በእምቦጭ መያዙ ማረጋገጡን ተናግረዋል፡፡

ባለፈው ክረምት ለመከላከል ጥረት ቢደረግም አረሙ በሐይቁ ላይ በእጥፍ መጨመሩን አስረድተዋል፡፡

ሐይቁን ከእምቦጭ አረም የመከላከል ስራ ከዞኑ አቅም በላይ መሆኑን ያስታወቁት  አቶ ዮሱፍ “አጥኝ ቡድን እንዲቋቋም ለሚመለክታቸው የክልልና የፌዴራል ተቋማት ጥያቄ ቀርቦ  ምላሽ እየተጠበቀ ነው “ብለዋል፡፡

አረሙ በሐይቁ ላይ በከፍተኛ ፍጥነት እየተስፋፋ በመሆኑ ለማስወገድ ባለ ድርሻ አካላትን ያሳተፈና በጥናት ላይ የተመሰረተ መፍትሔ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

የደቡብ ክልል አካባቢ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ቁጥጥር ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳሙኤል ቀቀቦ በበኩላቸው ሀይቁን ከእምቦጭ አረም የመከላከል የንቅናቄ ስራ በአጭር ጊዜ እንደሚጀመር አስታውቀዋል፡፡

በሀይቁ አዋሳኝ አካባቢ የተውጣጡ ዘጠኝ አባላት ያለው ቡድን በመጪው ሰኞ ወደ አማራ ክልል ባህር ዳር ከተማ አምርቶ የጣና የእምቦጭ አረም አወጋገድ ልምድ ቀስሞ እንደሚመለስ አመልክተዋል፡፡

የአባያ ሀይቅ ረግረጋማ አካባቢዎች አስቸጋሪነት፣ አዞን ጨምሮ የተለያዩ እንስሳት አደገኛነትና በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች አጋጥሞ የነበረው አለመረጋጋት በመከላከል ስራው ላይ እንቅፋት ሆኖ መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡

ከጣና እምቦጭን ለማስወገድ የተዘጋጁ ማሽኖች የአባያን ረግረጋማ ቦታዎች በምን አይነት መልኩ ለማስወገድ እንደሚቻል ልምድ የሚገኝበት መሆኑን አቶ ሳሙኤል ገልጸዋል፡፡

አረሙን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት የስምጥ ሸለቆ ሀይቆች ባለስልጣንና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በቅንጅት ሊንቀሳቀሱ እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

አርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ የተለያዩ ጥናቶችን ማድረጉን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ የአርባምንጭ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ አረሙን ማስወገጃ ጀልባ ሰርቶ ባለፈው ዓመት የሙከራ ስራ መጀመሩን አውስተዋል፡፡

አቶ ሳሙኤል እንዳመለቱት ከጣና ሀይቅ የሚገኘውን ተሞክሮ በመውሰድ ውጤታማ ስራ ለማከናወን ዝግጅት ተደርጓል፤ ባለፈው ዓመት በተደረገው የመከላከል ስራ ከ36 ሄክታር በላይ አረም ማጽዳት ተችሏል፡፡

በውስጡ ከ54 በላይ ብዝሃ ህይወት የያዘውና ከስምጥ ሸለቆ ሐይቆች በስፋቱ ቀዳሚ የሆነው አባያ ሐይቅ በአረሙ ከተጠቃ አንድ አመት ቢሆንም እስከአሁን ከሙከራ ውጭ አጥጋቢ የሆነ የመከላከል ስራ አለመከናወኑ ተመልክቷል፡፡