የአፍሪካ ህብረት አስቸኳይ ጉባኤ በቀጣዩ ሳምንት ይጀምራል

54
አዲስ አበባ ጥቅምት 29/2011 የአፍሪካ ህብረት የመሪዎችና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች አስቸኳይ ጉባኤ በመጪው ረቡዕ በአዲስ አበባ እንደሚጀመር የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ። ሚኒስቴሩ በጉዳዩ ዙሪያ በሰጠው መግለጫ፤ አስቸኳይ ጉባኤው በስኬት እንዲጠናቀቅ ኢትዮጵያ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች ማጠናቀቋን ገልጿል። የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ 11ኛውን የአፍሪካ ህብረት አስቸኳይ ጉባኤ በመሪዎችና በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ደረጃ ታከናውናለች። ህዳር 5 እና 6 ቀን 2011 ዓ.ም በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ደረጃ እንዲሁም ህዳር 8 እና 9 ቀን 2011 ዓ.ም በመሪዎች ደረጃ የሚከናወን መሆኑን ጠቁመዋል። የጉባኤው አጀንዳ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ማሻሻያን በተመለከተ ሲሆን፤ የ45 አገራት መሪዎች ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅም ገልጸዋል። በኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሰብሳቢነት በአገር አቀፍ ደረጃ ጉባኤውን ለማዘጋጀት 30 መስሪያ ቤቶች ያሉበት ብሔራዊ ኮሚቴ ፣13 መስሪያ ቤቶችን ያካተተ ብሔራዊ የኤርፖርት ኮሚቴ ተቋቁሟል። በተጨማሪም ሌሎች የውጭ ጉዳይ ንዑስ ኮሚቴዎች አስፈላጊ ግብዓቶችን በማሟላት ለጉባኤተኞቹ ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት እያደረጉ መሆኑን አቶ መለስ ጠቁመዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም