አብዴፓ የክልሉን ወጣቶችና ሴቶች ፖለቲካዊ ተሳትፎ ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ አስታወቀ

55
ሰመራ ጥቅምት 29/2011 የአፋር ብሔራዊ ዴሞክራሲዊ ፓርቲ (አብዴፓ) የክልሉን ወጣቶችና ሴቶች ፖለቲካዊ ተሳትፎ ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እንደሚሰራ አስታወቀ፡፡ የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበርና የርዕሰ-መስተዳድሩ የህዝብ ግንኙነት አማካሪ አምባሳደር ሀሰን አብዱልቃድር እንደገለጹት የተጀመረውን ሀገራዊ ለውጥ ለማስቀጠል በወጣቶችና በሴቶች ፖለቲካዊ ተሳትፎ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ይሰራል፡፡ ከክልሉ ህዝብ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ሴቶችና ወጣቶች መሆናቸውን የገለጹት አምባሳደር ሀሰን የምጣኔ ሀብትና ፖለቲካዊ ተሳትፏቸውን ለማረጋጋጥ በፓርቲው 7ኛ ድርጅታዊ ጉባኤ ተጨባጭ እርምጃዎችና ጠቃሚ ውሳኔዎች ይተላለፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ተናግረዋል፡፡ "ከምጣኔ ሀብት ተጠቃሚነት አንጻር የወጣቶችን ተዘዋዋሪ ፈንድ በመጠቀም ባላፈው ዓመት ከ3 ሺህ በላይ ሥራ አጥ ወጣቶችን በተለያዩ የሥራ ዘርፎች ተሰማርተው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ ተችሏል" ብለዋል። በተያዘው በጀት ዓመትም የብድር አግልግሎቱን የበለጠ ተደረሽ ለማድረግ ከከተማ ወጣቶች በተጨማሪ በገጠር የሚገኙ አርብቶ አደር ወጣቶች በእንስሳት ማድለብና በሌሎች አዋጭ የግብርና ሥራዎች ላይ እንዲሰማሩ ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡ አምባሳደር ሀሰን እንዳሉት የወጣቱን ፖለቲካዊ ተሳትፎ ከማረጋገጥ አኳያ በክልሉ ከሚገኙ ክፍተኛ የአመራር ቦታዎች ውስጥ ከ50 በመቶ በላይ የሚሆነው የኃላፊነት ቦታ በወጣቶች እንዲያዝ ተደርጓል፡፡ እውነታው ይህ ሆኖ ሳል ፓርቲውም ሆነ የክልሉ መንግስት ወጣቶችን ወደ አመራርነት እንደማያመጡ ተደረጎ የሚናፈሱ ወሬዎች መሰረተ-ቢስ መሆናቸውን አማካሪው ገልጸዋል። የተሻለ የትምህርት ዝግጅት፣ የመፈጸምና የማስፈጸም ብቃት ያላቸው አዳዲስ ወጣቶችን ከመቼውም ግዜ በተሻለ መልኩ ወደ አመራርነት እንዲመጡ መደረጉን አስረድተዋል፡፡ የክልሉን ሴቶች ወደ አመራርነት ከማምጣት አኳያ የአርብቶ አደሩ ሴቶች ስር የሰደደ የባህል ተጽዕኖ ቢኖርባቸውም ከክልል እስከ ወረዳ የተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች እንዲይዙ የተሰሩት ስራዎች የሚናቁ አለመሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ የሴቶች ተሳትፎ አሁንም ቢሆን ክፍተት ያለበት መሆኑን የጠቆሙት አምባሳደር ሀሰን በአብዴፓ 7ኛ ደርጅታዊ ጉባኤ በሚፈለገው ደረጃ ሴቶችን ወደአመራርነት ለማምጣት በቂ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡ የአፋር ብሔራዊ ዴሞክራሲዊ ፓርቲ (አብዴፓ) 7ኛ ድርጅታዊ ጉባኤ በህዳር ወር እንደሚካሄድ ይጠበቃል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም