ሊጉን የማይመጥነው የተጫዋቾች ክፍያ ክለቦችን አደጋ ውስጥ የሚከት ነው ተባለ

455

አዲስ አበባ ጥቅምት 29/2011 የኢትዮጵያ እግር ኳስ ተጫዋቾች ክፍያ ክለቦችን አደጋ ውስጥ የሚከት ነው ተባለ።

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የሚካፈሉ ክለቦች ለአንድ ተጫዋች በወር እስከ 256 ሺህ ብር መክፈላቸውን ካለፈው ዓመት የክለቦች ማህደር የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ለመጫወት የፈረሙ የውጭ ተጫዋቾች ክፍያ ደግሞ ከዚህም በላይ የናረ መሆኑ ታውቋል።

ይህ የተጋነነ ክፍያ የክለቦችን ዕጣ ፈንታ  የሚፈታተን በመሆኑ በቸልታ ሊታይ እንደማይገባ የተለያዩ ክለቦች አመራሮች ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ እግር ኳስ ክለብ ስራ አስኪያጅ አቶ ገዛኸኝ ወልዴ እንደሚሉት በኢትዮጵያ እግር ኳስ ተሳታፊ ክለቦች ለተጫዋቾች የሚከፍሉት ክፍያ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል።

ትልቁ ችግር ተጨዋቾቹ የሚያገኙት ክፍያ ማደጉ ሳይሆን ክለቦች ይህን ያህል ክፍያ ለመፈጸም የሚያስችል ገቢ የሚያመነጩ አለመሆናቸው ነው ይላሉ።

አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ክለቦች የተጫዋቾች ክፍያ ማሳደግ ላይ እንጂ ክለቡ ጠንካራ መሰረት እንዲኖረው የሚያደረጉ የእግር ኳስ መሰረተ ልማት ስራዎች እና ገንዘብ ማመንጨት ላይ ደካሞች ናቸው።

ብዙዎቹ ክለቦች ገንዘብ የሚያገኙት ከመንግስት ካዝና እንጂ የራሳቸው ቋሚ የገቢ ምንጭ የላቸውም።

በመንግስት በጀት ላይ የተንጠለጠሉ ክለቦች ደግሞ ድጎማው ቢቆምባቸው አደጋ ውስጥ የሚገቡ ናቸው ይላሉ አቶ ገዛኸኝ።

የአማራ ክልል ስፖርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ አዱኛ ግዛው የተጫዋቾች ክፍያ እና የአገሪቱ የእግር ኳስ እድገት ተመጣጣኝ እንዳልሆነ ነው ያነሱት።

የተጫዋቾች  ክፍያ በዚሁ የሚቀጥል ከሆነ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ተሳታፊ ክለቦች እጣ ፈንታ ላይ አደጋ መደቀኑንም ተናግረዋል።

በእግር ኳሱ የሚሳተፉ በርካታ ክለቦች ከሌሉ ደግሞ እድገቱን የሚያቀጭጭ እንደሆነ ነው የገለጹት።

የኦሮሚያ እግር ኳስ ቢሮ የጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍሮምሳ ለገሰ በበኩላቸው ችግሩ እንደሌሎች ሁሉ በኦሮሚያ የሚገኙ ክለቦች ላይ የሚስተዋል መሆኑን ተናግረው ብዙ ክለቦች ተጫዋቾች ከማሳደግ ይልቅ ማዘዋወር ላይ ነው የሚያተኩሩት ብለዋል።

በቀጣይ ክለቦች ከትምሀርት ቤት እና በሌሎች የፕሮጀክት የስልጠና ጣቢያዎች በመሳተፍ መስራት እንደሚያስፈግ ነው የተናገሩት።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሸን ምክትል ፕሬዝዳንት ኮሎኔል አወል አብዱራሂም ችግሩን ፌዴሽኑም እንደሚያውቀው ገልጸው በዚህ ዓመት የሊግ ኮሚቴው ከሚመለከታቸው ጉዳዮች አንዱ ይህ ይሆናል ሲሉ አመልክተዋል።

ከሁለት ሳምንታት በፊት የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ባስጠናው ጥናት መሰረት በኢትዮጵያ የሚገኙ እግር ኳስ ክለቦች የራሳቸው የመለማመጃና የመጫወቻ ሜዳ፣ ታዳጊ ቡድኖች መያዝና ሌሎችም መስፈርቶች አሟልተው አልተገኙም።