አንድ የሆነች ኢትዮጵያን ለመገንባት “የእኔ ብቻ” የሚለው አስተሳሰብ መስተካከል አለበት

80
ድሬዳዋ  ጥቅምት 29/2011 አንድ የሆነች ኢትዮጵያን ለመገንባት “የእኔ ብቻ” የሚለው አስተሳሰብ መስተካከል እንዳለበት እና በአሁኑ ወቅት አገሪቱ የሚያስፈልጋት ሰላም እንደሆነ ተገለጸ። አምስት የምስራቅ ኢትዮጵያ ክልሎችን በማሳተፍ በድሬዳዋ አስተዳደር ሲካሄድ የነበረው የሰላም ኮንፍረንስ ተጠናቋል። መድረኩን የፌዴሬሽን ምክር ቤት ከኦሮሚያ፣ ሶማሌ፣ አፋር፣ ሃረሪ ክልሎችና ድሬዳዋ አስተዳደር ጋር በመተባበር ''ብዘሃነት፣ መቻቻልና እርቅ ለአገር አንድነት'' በሚል መሪ ሃሳብ ያዘጋጀው። የኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች ላነሷቸው የተለያዩ ጥያቄዎች የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ በሰጡት ምላሽ ተጠናቋል። በውይይታቸውም ከአካባቢያቸው ጀምሮ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች ህብረተሰቡ የሃይማኖት፣ ባህል፣ ቋንቋና ሌሎች ልዩነቶችን በማቻቻል አብሮ መኖሩን አንስተዋል። በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ እየታየ ያለው ግጭትና እየተፈጠረ ያለው በሃይማኖት፣ በብሔርና በቋንቋ የማለያየት ሙከራ ለፖለቲካ ፍጆታ ተብሎ የተፈጠረ ሴራ መሆኑን ተሳታፊዎች ተናግረዋል። ለዚህም ቀደም ሲል በድንበር አካባቢ በግጦሽ መሬት ይፈጠር የነበረው ግጭት አሁን መልኩን እየቀየረ በሌሎችም አካባቢዎች እየተዛመተ መሆኑን እንደ ምሳሌ አንስተዋል። በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች እየተከሰተ ያለው ግጭት አብረው የሚኖሩ ህዝቦች የፈጠሩት አለመሆኑን ተናግረዋል። ሰላምን ለማረጋገጥ ምክክሮች በተለያየ ጊዜ እየተደረገ ቢሆንም በተጨባጭ ለውጥ አለመምጣቱን የተናገሩት ተሳታፊዎቹ ውጤት ለማምጣት የሚያስችል ጥናት ተደርጎ በየደረጃው ተግባራዊ መሆን እንዳለበት ጠቁመዋል። መንግስት ሰላምን ለማስከበር እየወሰደ ያለው ተነሳሽነት ዝቅተኛ ነው የሚሉ ሃሳቦችም ተንጸባርቀዋል። በአዲስ አበባ ዩኒቨስርቲ የጥናትና ምርምር ተቋም ዋና ዳይሬክተር ፕሮፌሰር አህመድ ዘካሪያ በሰጡት አስተያየት በተለያዩ አካባቢዎች እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶች መንስዔ በጎሳ ላይ የተመሰረተ የመንግስት አወቃቀር እንደሆነ ገልጸዋል። የጎሳ ፖለቲካ ቅኝ ገዥዎች ለአፍሪካ ትተውት የሄዱት የአፍሪካን የተፈጥሮ ሃብት መጠቀሚያ ስልት መሆኑንም ፕሮፌሰሩ አብራርተዋል። በመሆኑም ኢትዮጵያውያን ከጎሳ መረብ ውስጥ ወጥተው የአገሪቱን የተፈጥሮ ሃብት በአግባቡ በመጠቀም ወደሃብት በመለወጥ ራሳቸውን መለወጥ እንደሚገባቸው ጠቁመዋል። ሰላምን ከቤተሰብ ጀምሮ በመስበክና መንግስት ለወጣቱ የስራ እድል በመፍጠር እንዲሁም የተለያዩ የአለም አገሮችን እያለሙ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ምሁራን ወደ አገራቸው መጥተው የሚሰሩበት ምቹ ሁኔታ መፈጠር እንዳለበት አመልክተዋል። ሌሎች በመድረኩ የተሳተፉ ባለሙያዎችም ሰላም ከምንጊዜውም በላይ አስፈላጊ በመሆኑ የሁሉንም ኢትዮጵያውያንን ጥረት እንደሚያሻ አጽንኦት ሰጥተዋል። የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሂም ሰላም የማስፈን ጉዳይ የሁሉም ዜጋ ኃላፊነት እንደሆነ ገልጸዋል። መንግስት የሚያከናውናቸውን የልማት ስራዎች ማገዝና ጥፋት ሲኖርም በመመካከር መፍትሄ ለማምጣት ህዝቡ ከመንግስት ጎን እንዲሆን ጠይቀዋል። ''እኛና እናንተ'' የሚለውን መለያየት በመተው ሁሉም ዜጋ እርስ በርስ እየተጠቋቆመ ችግር ውስጥ ከመግባት ይልቅ በመተባበር መስራት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል። 'የእኔ ብቻ' የሚለውን በመተው 'የእኛ' የሚለውን አስተሳሰብ ማዳበር እንደሚገባም ጠቁመዋል። ዘር፣ ሃይማኖት፣ ብሄር በመቁጠር ችግሮችን ወደሌሎች ከመግፋት ይልቅ ወደራስ መመልከት ሰላምን ሊያረጋግጥ እንደሚችል አፈ ጉባዔዋ ተናግረዋል። ''መንግስት ህዝቡን ማዳመጥ አለበት ታች ድረስ መስራት አለበት'' ተብለው የተነሱ ሃሳቦች ትክክል መሆናቸውን በማንሳት ህዝቡም ለመርዳትና አብሮ ለመስራት ዝግጁ መሆን አለበት ሲሉ ገልጸዋል። አፈ ጉባኤዋ የልማት ፍትሃዊነት የለም የሚለው ሃሳብ ትክክል መሆኑን ገልጸው ሰላምን የማረጋገጥ ጉዳይ ቀዳሚ እንደሆነ አስገንዝበዋል። በመሆኑም በቀጣይ ከወረዳ ጀምሮ የሚመለከታቸው የመንግስት አካላት ከህዝብ ጋር የተነሱ ችግሮችን እንዲፈቱ በማስገንዘንብ ''ሰላም ካለ ያለችን ኢትዮጵያ ለሁሉም ትበቃለች'' ሲሉ አንስተዋል። የሰላም ኮንፈረንሱ ባለ ሰባት ነጥብ የአቋም መገለጫ በማውጣትና በሃይማኖት አባቶች ምርቃት ተጠናቋል። ተመሳሳይ የሰላም መድረኮች በቀጣይም በተለያዩ አካባቢዎች እንደሚካሄድ ተጠቁሟል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም