የእቀባ እርሻን መተግበራችን ምርታችንና ገቢያችን እንዲጨምር አድርጓል-አርሷደሮች

86
አዲስ አበባ ጥቅምት 28/2010 የእቀባ አስተራርስ ዘዴ ምርትና ምርታማነታቸውን በማሳደጉ ገቢያቸው መጨመሩን የወላይታ ዞን አርሶ አደሮች ተናገሩ። የእቀባ እርሻ ቴክኖሎጂ የአፈርን ጤንነት በማሻሻል፣ አካባቢን በመጠበቅና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ዘላቂ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ የሚያስችል የአስተራረስ ዘዴ ነው። ቴክኖሎጂውን በዞኑ ያስተዋወቀው የጠረጴዛ ልማት ማህበር የተሰኘ አገር በቀል ግብረ ሰናይ ድርጅት የእቀባ እርሻው የተተገበረባቸውን የሁምቦ፣ ኦፋ፣ ኪንዶ ኮይሻና ዳሞት ወይዴ ወረዳዎች እንቅስቃሴ ለባለድርሻ አካላት አስጎብኝቷል። የእቀባ አስተራረስ ዘዴን በመተግበራቸው ምርትና ምርታማነታቸው ማደጉን የገለጹትና ኢዜአ ያነጋገራቸው የአካባቢው አርሶ አደሮችም  የእርሻ መሬታቸው ለምነቱ መጠበቁን ይናገራሉ። አርሶ አደር መሰለ ማዴቦ እንዳሉት ቴክኖሎጂውን በመጠቀም የተሸለ ምርት ማግኘት ጀምረዋል፤ ሌሎች አርሶ አደሮችም የእርሳቸውን ውጤታማነት እያዩ ፈለጋቸውን መከተል ጀምረዋል፡፡ አርሷደር አስቴር ጎአም እንዳሉት ደግሞ አሁን የሚተገብሩት የአስተራረስ ዘዴ ቀላልከመሆኑም በተጨማሪ የተሸለ ምርት እንዲያገኙአግዟቸዋል፡፡ ሌላው ሴት አርሶ አደር ፈለቀች ተካ ዘዴውን መተግበር ከጀመሩ ሁለተኛ ዓመት እንደሆናቸውና ምርታቸው በመጨመሩ ኑሯቸው መሻሻሉን ተናግረዋል። ዘዴው ጉልበት የማይፈጅና በቀላሉ የሚታረስ በመሆኑ 'ለሴት አርሶ አደሮች እፎይታን ፈጥሯል' ነው ያሉት። በወረዳቸው የእቀባ እርሻን በመሞከር የመጀመሪያዋ እንደሆኑ የገለጹት ሴት አርሶ አደር አስናቀች ጋኦሻ የአካባቢው አርሶ አደር ዘዴውን ለመጀመር እምነት ባልነበረው ወቅት በድፍረት መጀመራቸው ተጠቃሚ እንዳደረጋቸውና ለማህበረሰቡ ተምሳሌት በመሆናቸው ደስተኛ እንደሆኑ ነው የገለጹት። አርሷደር አስናቀች ከማሳቸው በሚገኙት ምርት ልጆቻቸውን ያስተምራሉ፤ የቤተሰባቸውን ቀለብም ይሸፍናሉ፡፡ የ100 ዓመት እድሜ ባለጸጋው አርሶ አደር ሞጃ መገልቾ ጎረቤቶቻቸውና ልጆቻቸው በቀላሉ ምርት ሲሰበስቡ በማየታቸው እርሳቸውም በዚሁ የአስተራረስ ዘዴ መሬታቸውን መሸፈናቸውን ገልጸው አሰራሩ ቀላልና ምቹ በመሆኑ ከድካም መገላገላቸውን ተናግረዋል፡፡ ፕሮጀክቱን አርሷደሩ ጋር በማውረድ አሰራሩ እንዲሰርጽ ያደረገው በዞኑ ድጋፍ የሚሰጠው የጠረጴዛ ልማት ማህበር ስራ አስኪያጅ አቶ በረከት ጣሰው በበኩላቸው ዘዴው በተመረጡ ቦታዎች ሙከራ ተደርጎ ውጤታማነቱን ማረጋገጥ ተችሏል ብለዋል። በዚህም ፕሮጀክቱን ለማስፋፋት የማህበሩ አቅም ውስን በመሆኑ የተለያዩ መንግስት በባለቤትነት ተቀብሎ እንዲያስቀጥለው  ጠይቀዋል። ይሁን እንጂ አሰራሩን ከመንግስት ጎን በመሆን ባላቸው አቅምና እውቀት ማህበረሰቡን ብሎም አካባቢውን የማገልገል ተግባራቸው ቀጣይ እንደሚሆንም አብራርተዋል። ግብርና ሚኒስቴር በበኩሉ የእቀባ እርሻ ቴክኖሎጂ ከአገሪቱ አካባቢያዊ ሁኔታ አንጻር አዋጭ በመሆኑ በተያዘው ዓመት በባለቤትነት ተረክቦ ተግባሩን በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች ተደራሽ እንደሚያደርግ ገልጿል። በሚኒስቴሩ የአፈር ለምነት ማሻሻያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ተፈራ ሰለሞን እንዳሉት የእቀባ እርሻ በተጀመረባቸው አካባቢዎች ያለው የምርት መጠን ከፍተኛ መሆኑን በመስክ ምልከታ ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል። በወላይታ ዞን ሁምቦ፣ ኦፋ፣ ኪንዶ ኮይሻና ዳሞት ወይዴ ወረዳዎች የእቀባ እርሻን የተገበሩ ከ11 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች ተጠቃሚ መሆን ችለዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም