በኦሮሚያ የአፈር አሲዳማነትን ለመቀነስና ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ እየተሰራ ነው

79
አዳማ ጥቅምት 28/2011 በኦሮሚያ ክልል የአፈር አሲዳማነትን ለመቀነስና ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ የአርሶ አደሩን የይዞታ ባለቤትነት ማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን   የክልሉ የገጠር መሬት አጠቃቀምና አስተዳደር ቢሮ ገለጸ። የቢሮው ምክትል ኃላፊ አቶ ሚሬሣ ፊጤ ለኢዜአ እንደገለጹት የአርሶ አደሩን የመሬት ባለቤትነት ለማረጋገጥና ሙሉ ዋስትና ለመስጠት አሉታዊ ተፅእኖ እየፈጠረ ያለውን አሲዳማነትን መቀነስ ሚናው የላቀ ነው። በክልሉ በየዓመቱ ከሚታረሰው ስድስት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሄክታር የሚሆነው በአሲድ እንደሚጠቃና በዚህም ምርትና ምርታማነት ከ50 እስከ 60 በመቶ እንደሚቀንስ አስረድተዋል። በአሲዳማ መሬት በተጠቃ መሬት አርሶ አደሩ የግብርና ግብዓቶች ተጠቅሞ ለማልማት ቢሞክርም፤ ውጤታማ እንደማይሆን የገለጹት ምክትል ኃላፊው፣ የመሬቱን ለምነት ለመመለስ በኖራ፣ በፍግና በተፈጥሮ ማዳበሪያ እየታከመ መሆኑንም አመልክተዋል። በዚህ ዓመት ከ300ሺህ ሄክታር በላይ በኖራና በተፈጥሮ ማዳበሪያ ለማከም 14 አዳዲስ የኖራ መፍጫ ፋብሪካዎችን አሲዳማነት በበዛባቸው አካባቢዎች በመቋቋም ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል። በተለይም በአራቱ ወለጋ፣በምሥራቅ፣ምዕራብና ሰሜን ሸዋ፣አርሲና ባሌ፣ጅማና ኢሉ አባቦራ፣ቦረናና ጉጂ አካባቢዎች ላይ ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል። በዘላቂነት የመሬት ለምነትን ለመጠበቅ በዚህ ዓመት የአርሶ አደሩን የይዞታ ባለቤትነት ለማረጋገጥ የእርሻ ማሳ ካርታ የመስጠት ሥራ 80 በመቶ ለማድረስ እየተሰራ መሆኑን አቶ ሚሬሳ ተናግረዋል። እስካሁን ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ አርሶ አደሮች ማሳ ተለክቶ የይዞታ ማረጋገጫ ከ400ሺህ በላይ ለሚሆኑ ባለቤቶች ካርታ መሰጠቱን አመልክተዋል። በምሥራቅ ሸዋ ዞን አዳማ ወረዳ የቆቦ ሉጦ ቀበሌው አርሶ አደር ቃቻ ጠሊላ ካላቸው ሰባት ሄክታር መሬት ውስጥ በአሲድ የተጠቃውን ሁለት ሄክታር መሬትበ40 ኩንታል አክመው 70 ኩንታል ጤፍ ማግኘታቸውን ተናግረዋል። በመኸር ወቅት ከዘሩት ስንዴና ሽንብራ ከአምና የተሻለ ምርት እንደሚጠብቁም አስታውቀዋል። መሬታቸው በአሲድ በመጠቃቱ በሄክታር ከሦስት ኩንታል የማይበልጥ ምርት ያገኙ እንደነበርና ዘንድሮ መሬታቸውን በኖራ በማከም 60 ኩንታል በቆሎ ማግኘታቸውን የገለጹት በምሥራቅ ሸዋ ዞን የአዳሚ ቱሉ ጅዶ ኮምቦልቻ ወረዳ የኢዶ ጎጆላ ቀበሌ አርሶ አደር ከድር ኢሬሶ ናቸው።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም