ሁለተኛው አገር አቋራጭ የአትሌቲክስ ሻምፒዮና በሱሉልታ ይካሄዳል

591

አዲስ አበባ ጥቅምት 28/2011 ሁለተኛው የክልሎች ፣ ከተማ አስተዳደሮች ፣ ክለቦችና ተቋማት አገር አቋራጭ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ህዳር 2 ቀን 2011 ዓ.ም በሱሉልታ ይካሄዳል።

ውድድሩ በሱሉልታ፣ ከታ ወሌሌና ወሌሉቤ ቀበሌ እሁድ ከጠዋቱ አንድ ሠዓት ጀምሮ እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ዛሬ አስታውቋል።

በአዋቂዎች ምድብ ወንዶች 12 ኪሎ ሜትር ፣ ሴቶች 8 ኪሎ ሜትር፣ በድብልቅ ሪሌይ ሁለቱም ጾታ የ8 ኪሎ ሜትር እንዲሁም አንጋፋ አትሌቶች የ8 ኪሎ ሜትር ውድድሮችን ያካሂዳሉ።

በዚህ ውድድር 92 ሴት፣ 177 ወንድ አትሌቶች እንደሚካፈሉ የፌዴሬሽኑ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ቢልልኝ መቆያ ገልጸዋል።

የግልና አንጋፋ አትሌቶችን ጨምሮ 18 ቡድኖች የተመዘገቡ ሲሆን የውድድሩ ዓላማም ክልሎች፣ ከተማ አስተዳደሮች፣ ክለቦችና ተቋማትን በአገር አቋራጭ ውድድር በማሳተፍ ለተተኪ አትሌቶች ዕድል መፍጠር ነው።

የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የውድድርና ተሳትፎ ሥራ ሂደት መሪ አቶ አስፋው ዳኜ ከታዋቂ አትሌቶች ታዬ ግርማና ገብሬ እርቅይሁን ከኦሮሚያና አማራ ክልሎች ተስፋዬ ድሪባ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ያሲን ሃጂና ሃይማኖት አለሙ ከፌዴራል ማረሚያ ቤቶች ስፖርት ክለብ እንደሚሳተፉ ገልጸዋል።

ከሴቶች አትሌት ፋንቱ ወርቁ ከኦሮሚያ፣ ሃዊ አለሙና አለሚቱ ሃዊ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ ገበያነሽ አየለና ሃዊ ፈይሳ ከመከላከያና ብርቱካን አዳሙ ከኢትዮ-ኤሌክትሪክ ስፖርት ክለብ ይሳተፋሉ።

በአዋቂ ምድብ 12 ኪሎ ሜትር በሁለቱም ጾታዎች በቅደም ተከተል ከአንደድ እስከ ሶስተኛ ለሚወጡ አትሌቶች የ12፣ የ9 እና የ7 ሺህ ብር ሽልማት እንደሚበረከት ተገልጿል።

ለሁሉም ምድብ አሸናፊዎች የሜዳሊያና የማበረታቻ የገንዘብ ሽልማት የሚበረከት ሲሆን ፌዴሬሽኑ 150 ሺህ ብር ለሽልማት ማዘጋጀቱን ከፌዴሬሽኑ የኮሙኒኬሽን የስራ ሂደት ክፍል የተገኘው መረጃ ያመለክታል።