ነዋሪዎቹ ለቀብሪ ደሃር ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች አቀባበል ለማድረግ መዘጋጀታቸውን አስታወቁ

77
ጅግጅጋ ጥቅምት 28/2011 የቀብሪ ደሃር ከተማ ነዋሪዎች በዚህ ዓመት ወደ ዩኒቨርሲቲው ለሚመጡ ነባርና አዲስ ተማሪዎች አቀባበል ለማድረግ መዘጋጀታቸውን ዛሬ ገለጹ። ዩኒቨርሲቲው ከከተማው ነዋሪዎችና ባለድርሻ አካላት ጋር በ2011 ትምህርት ዘመን የተማሪዎች አቀባበልና የመማር ማስተማር እንቅስቃሴ ሰላማዊ ሆኖ በሚሆንበት ጉዳይ ላይ ተወያይቷል። የቆራሃይ ዞን አገር ሽማግሌዎች ተወካይ አቶ መሐመድ ዑመር ወደ ዩኒቨርሲቲው የሚመጡ ተማሪዎችን በፍቅር ተቀብለን ባህላችንን እንዲያውቁ እናደርጋቸዋለን ብለዋል። የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎችና ምሁራን ለአገሪቱ ሕዝቦች አብሮነት የላቀ አስተዋፅኦ እንዳላቸውም አመልክተዋል። በሳይንስና ከፍተኛ ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ሱፐርቪዥን ቡድን አባል አቶ በሱፈቃድ ኃይለማርያም በዩኒቨርሲቲው ሰላማዊ የመማር ሂደት ለመፍጠር የከተማው ማህበረሰብ የማይተካ ሚና እንዳለው ገልጸዋል። በዩኒቨርሲቲው የሚንፀባረቁት የፖለቲካ አመለካከት ለግጭት መንስዔ እንዳይሆኑ መሥራት ይገባል። ዩኒቨርሲቲው ነባር ተማሪዎቹን ከነገ ጀምሮ መቀበል ይጀምራል። 1500 አዲስ ተማሪዎች በሚቀጥለው ወር መግቢያ ላይ ለመቀበልም ተዘጋጅቷል። ዩኒቨርሲቲው ባለፈው ዓመት 1ሺህ 200 ተማሪዎችን በመቀበል ሥራ ጀምሯል። የቀብሪ ደሃር ዩኒቨርሲቲ በአራት ኮሌጆችና በ11 የትምህርት ክፍሎች አማካይነት አገልግሎቱን ይሰጣል።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም