የሪያድና አካባቢው የትግራይ ልማት ማህበር አባላት ለተፈናቀሉ የክልሉ ተወላጆች ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አደረጉ

51
መቀሌ ጥቅምት 28/2011 የሪያድና አካባቢው የትግራይ ልማት ማህበር ቅርጫፍ አባላት ከተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ለተፈናቀሉ የትግራይ ክልል ተወላጆች ከአንድ ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ አደረጉ። አባላቱ ድጋፉን ያደረጉት ‘‘የቁርጥ ቀን ወገን‘‘ በሚል መሪ ቃል የገንዘብ ማሰበሳቢያ ፕሮግራም በማዘጋጀት ነው። በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች በተፈጠረው ሁከትና ግርግር ምክንያት  ለተፈናቀሉ የክልሉ ተወላጆች  ድጋፍ እንዲውል ያሰባሰቡትን አንድ ሚሊዮን 55 ሺህ ብር  የክልሉ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ በከፈተው የባንክ ሂሳብ ቁጥር ገቢ አድርገዋል፡፡ የቢሮው ህዝብ ግንኙነት አስተባባሪ መምህር ሰሎሞን ገብረህይወት ዛሬ ለኢዜአ እንዳሉት የቅርንጫፍ ማህበሩ አባላት የጀመሩትን ድጋፍ በቀጣይም አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ለቢሮው በጻፉት ደብዳቤ አረጋግጠዋል፡፡ የትግራይ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ከተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች የተፈናቀሉ ወገኖችን ለማቋቋም የሚያግዝና ለአንድ ዓመት የሚቆይ የገንዘብ ማሰባሰቢያ ፕሮግራም በሃገር ውስጥና በውጭ እያካሄደ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች በተፈጠረው ሁከትና ግርግር ምክንያት የተፈናቀሉ 60 ሺህ የሚጠጉ የትግራይ ክልል ተወላጆች ወደ ትውልድ ቀያቸው መግባታቸውን መምህር ሰሎሞን ጨምረው ገልፀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም