የግብርና ሚኒስቴር የእቀባ አስተራርስ ቴክኖሎጂን በሁሉም የአገሪቷ አካባቢ አርሶ አደሮች ተደራሽ ሊያደርግ ነው

1340

አዲስ አበባ ጥቅምት 28/2011 የእቀባ አስተራርስ ቴክኖሎጂን በባለቤትነት በመምራት ለሁሉም አርሶ አደሮች ተደራሽ ለማድረግ ቅድመ ዝግጅት ማጠናቀቁን ግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ ቴክኖሎጂውን እየተገበሩ ከሚገኙ ድርጅቶች ጋር ለመምከርና የልምድ ልውውጥ ለማድረግ በወላይታ ዞን በሚገኙ የዕቀባ አስተራረስ ዘዴው በሚተገበርባቸው ወረዳዎች የመስክ ምልክታ እያደረገ ነው።

በሚኒስቴሩ የአፈር ለምነት ማሻሻያ ዳይሬክተር አቶ ተፈራ ሰለሞን ለኢዜአ እንደተናገሩት በአሁኑ ወቅት ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ የሚከሰት ድርቅ፣ የአፈር እርጥበት እጥረትና ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ የእርሻ ምርታማነት እንዲቀንስ እያደረገ ነው።

የእቀባ እርሻ ዘዴ የአፈር ጤንነትን በማሻሻል፣ አካባቢን በመጠበቅና ምርትና ምርታማነት በማሳደግ ዘላቂ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የሚያስችል የአስተራረስ ዘዴ ነው።

ነገር ግን ቴክኖሎጂው የሚተገብረው በተለያዩ ድርጅቶች አማካኝት መሆኑ የአስተራረስ ተግባሩ በተቀናጀ መንገድ እንዳይከናወንና ውጤታማ እንዳይሆን እንቅፋት ሆናል ብለዋል።

የአፈር ለምነትን በመጠበቅና የአርሶ አደሩን ጉልበት በመቆጠብ የግብርና ምርትን በብዛትና በጥራት ማምረት የሚያስችል የዕቀባ ቴክኖሎጂን በሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች ለማስረጽ፤ በኤክስቴንሽን ስርዓት መደበኛ ፕሮግራም ውስጥ እንዲገባ አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት መጠናቀቁን ተናግረዋል።

በተጨማሪም በመደበኛነት የሚከናወነው የምርጥ ዘርና ማዳበሪያ አቅርቦት በማሻሻልና አርሶ አደሩን ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን እንዲጠቀም በማድረግ አገሪቷ ከዘርፉ ለማግኘት የሚጠበቅባትን ጥቅም እንድታገኝ ማድረግ እንደሚገባ ገልጸዋል።

የዕቀባ አስተራረስ ዘዴን እየመራ ያለው የጠረጴዛ ልማት ማህበር የተሰኘ አገር በቀል ግብረ ሰናይ ድርጅት ፕሮግራም ማናጀር አቶ መስፍን ማቴዎስ፤ ማህበሩ ሰብዓዊ እርዳታና መልሶ ማቋቋም ላይ በስፋት የሚሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

የተጎዱ መሬቶችን መልሶ ማልማትና በግብርናው ዘርፍ የተሻሻሉ ዝርያዎችን ለአርሶ አደሩ ማስተዋወቅና የእቀባ እርሻ ዘዴን ማስፋት ላይ ሲሰራ መቆየቱን ገልጸው፤ ለበርካታ አርሶ አደሮች የስልጠና ድጋፍ በመስጠት ውጤታማ እንዲሆኑ አስችሏል ነው ያሉት።

ማህበሩ የእቀባ አስተራረስ ዘዴን ባስጀመረባቸው በወላይታ ዞን በሚገኙ የሁምቦ፣ ኦፋና፣ ኪንዶካይሻና ዳሞትወይዴ ወረዳዎች የመስክ ምልከታ የሚደረግ ሲሆን ጉብኝቱ ቴክኖሎጂው ባልተዳረሰባቸው ወደሌሎች አርሶ አደሮች ተሞክሮውን ለማስፋት እድል ይፈጥራል ብለዋል።

ማህበሩ በባለቤትነት ይመራው የነበረውን የዕቀባ ቴክኖሎጂ ለግብርና ሚኒስቴር ከማስተላለፉ በተጨማሪ ከተለያዩ ባለድረሻ አካላት ጋር በመስራት የእቀባ እርሻን ለማስረጽና ምርትና ምርታማነትን ለማረጋገጥ በቀጣይነት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።