በወላይታ ዞን የቢጫ ወባ ወረርሽኝ ተከሰተ - ኢዜአ አማርኛ
በወላይታ ዞን የቢጫ ወባ ወረርሽኝ ተከሰተ
69
አዲስ አበባ ጥቅምት 28/2011 በደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ውስጥ በወላይታ ዞን የቢጫ ወባ ወረርሽን መከሰቱን የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ። ኢንስቲትዩቱ ከተለያዩ አገር አቀፍና ዓለም ዓቀፍ የጤና ተቋማት የተውጣጣ የባለሙያዎች ቡድን ተቋቁሞ የመከላከል ስራዎች እያተከናወነ መሆኑን አስታውቋል። ኢንስቲትዩቱ ለኢዜአ በላከው መግለጫ እንደገለጸው፤ ከነሐሴ 5 ቀን 2010 ዓ.ም እስከ ጥቅምት 16 ቀን 2011 ዓ.ም 35 ሰዎች በቢጫ ወባ ወረርሽን መያዛቸውንና በምርመራ ቢጫ ወባ መሆኑ ባይረጋገጥም ሰዎች ለህለፈት ተዳርገዋል። በሴኔጋል ዳካር በተደረገ የላቦራቶሪ ምርመራም የቢጫ ወባ አምጭ ቫይረስ መኖሩ ማረጋገጡን ገለጾ፣ የፈጣን ምላሽ ሰጭ የባለሙያዎች ቡድን ተቋቁሞ የበሽታ ቅኝትና የቫይረሱ ተሸካሚ በሆኑ ትንኞችን የመከላከልና የምርመራ ስራ እየተከናወነ መሆኑን ነው ያስታወቀው። የበሽታውን ስርጭት ለመከላከልም በዞኑና በአጎራባች ወረዳዎች በሚገኙ የኃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎችና የጎሳ መሪዎችን ያቀፈ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን በመግለጫው ጠቁሟል። በወረርሽ በተጠቁና ለአጎራባች 7 ቀበሌዎች ለስምንት ተከታታይ ቀናት ከ31 ሺህ በላይ ክትባቱ ለሚያስፈልጋቸው ዜጎች መስጠቱን ኢንስቲትዩቱ ገልጿል። በቀጣይም በጋሞ ጎፋ ዞን ውስጥ በሚገኙ አጎራባች ወረዳዎች ለሚኖሩ ዜጎች ክትባቱን ለመስጠት አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ማድረጉን አመልክቷል።