የሚፈጠሩ ግጭቶችን ለማስቆም መንግስትና የሃይማኖት ተቋማት የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተገለጸ

63
አዲስ አበባ ጥቅምት 28/2011 ቀውሶችን በመፍታት በኢትዮጵያ ሰላምና አንድነትን ለማጠናከር መንግስትና የኃይማኖት ተቋማት የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተጠቆመ። የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዛሬ በወቅታዊ ግጭቶችና መፍትሄዎቻቸው ላይ እየመከረ ይገኛል። የጉባኤው የቦርድ ሰብሳቢ ንቡረ-ዕድ ኤልያስ አብርሃ በዚሁ ጉባኤ ላይ እንደገለፁት ለዘመናት ዘልቆ የቆየው በሃይማኖቶችና በዘር ልዩነት መካከል የነበረው ተከባብሮ የመኖር እሴት አሁን ላይ በብዙ ችግሮች እየተሸረሸረ ይገኛል። ለአብነትም የችግሮቹ መነሻ የኃይማኖት፣ የዘር፣ የኢኮኖሚና የማህበራዊ ልዩነቶች መሆናቸውን በመግለፅ እነዚህን ልዩነቶች የማባባስ ስራ በማህበራዊ ሚዲያው በዘመቻ እየተካሄደ ይገኛል ብለዋል። ልዩነቶችን መሰረት ያደረጉ ግጭቶች አንዱን ሰው በማንነቱ ብቻ ሲጠቀሙበት በሌላ በኩል ደግሞ ሰው በሰውነቱ ብቻ መጠቀም ያለበትን ሲከለክሉ ማየት ልምድ እየሆነ መጥቷል ሲሉም ተናግረዋል። የሃይማኖት ተቋማትና መሪዎቻቸው ታዲያ ለተከታዮቻቸው እነዚህን በቃልና በፅሁፍ የሚረጩ የሃሰት መረጃዎችን እንዳይቀበሉ የማስተማርና ተከታዮቻቸውም ቤተሰቦቻቸውም ከነዚህ ነገሮች ተከልክለው ለሰላምና አንድነት የድርሻቸውን ለመወጣት እንዲሰሩ ማድረግ አለባቸው በማለት አሳስበዋል። በመድረኩ  ሁለት ዕሁፎች ለውይይት የቀረቡ ሲሆን ኢትዮጵያ በቀደመው ዘመን የነበራትና የመቻቻል እሴት የዳሰሱና አሁን ላሉት ግጭቶች መፍትሄ ይሆናሉ ያሉትን ምክረ ሃሳቦች ያስቀመጡ ነበሩ። በዕሁፎቹ እንደተገለፀው ሰው ከማንም ጋር በፍቅርና በሰላም እንዲኖር የሁሉም ሃይማኖቶች አስተምህሮ ቢሆንም ከሃይማኖት መላላትና ከሃሰተኛና ቀስቃሽ መረጃዎች መበራከት ምክንያት አብሮነት እየጠፋ ግጭቶች እየተበራከቱ መጥተዋል። እነዚህ ግጭቶች ክቡር የሆነውን የሰውን ልጅ ህይወት እየቀሙና እያፈናቀሉ የአገር ሰላምን አደጋ ላይ እየጣሉ እንደሚገኙ ዕሁፎቹ በሰፊው አትተዋል። የጉባኤው ዋና ፀሃፊ መጋቢ ዘሪሁን ደጉ እንደገለፁት ከሃይማኖትና ከዘር ልዩነት በተጨማሪም የስራ አጥነት፣ ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል አለመኖርና የዴሞክራሲ አለመስፋፋት ለግጭቶቹና ልዩነቶቹ ምክንያት መሆናቸውንም በፅሁፎቹ ገልጸዋል። ለአንድነቱ መሸርሸርና ለሰላም እጦት ሃሰተኛ መረጃ በሚያወጡ ግለሰቦች ላይ መንግስት ህጋዊ እርምጃ መውሰድ እንዳለበትም ጠቁመዋል። የሃይማኖት መሪዎችም የሚናገሩትን በተግባር ለተከታዮቻቸው በማስተማር ከአመፅ ይልቅ በመነጋገርና በመወያየት የሚያምን ትውልድ በማፍራት ዘላቂ አንድነትና ሰላም ለማረጋገጥ መስራት እንዳለባቸው ተገልጿል። ትምህርት ቤቶችንም ጥሩ የሰብዕና መገንቢያ ከማድረግ አንፃር መምህራን አርአያነት እንዲላበሱ መንግስት ግዴታውን እንዲወጣም ምክረ ሃሳብ ቀርቧል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም