የሁለተኛ ሳምንት የፕሪሚየር ሊግ ቀሪ ጨዋታዎች ተራዘሙ

121
አዲስ አበባ ጥቅምት 28/2011 የሁለተኛው ሳምንት የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ቀሪ ጨዋታዎች በብሔራዊ ቡድን ዝግጅት ምክንያት ተራዘሙ። ለ2019ኙ የካሜሩን አፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ የምድብ ማጣሪያ ላይ የሚገኘው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ህዳር 9 ቀን 2011 ዓ.ም በአዲስ አበባ ስታዲየም ከጋና አቻው ጋር ይጫወታል። በሌላ ዜና በጃፓን ቶኪዮ በሚካሄደው ከ23 ዓመት በታች የኦሎምፒክ እግር ኳስ ውድድር ማጣሪያ የኢትዮጵያ ወንዶች ከ23 ዓመት በታች ኦሎምፒክ ብሔራዊ ቡድን የመጀመሪያ የቅድመ ማጣሪያ ውድድሩን ከሶማሊያ አቻው ጋር ህዳር 5 ቀን 2011 ዓ.ም ያካሂዳል። በሁለቱ ብሔራዊ ቡድኖች ውስጥ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ሰባት ክለቦች ሶስትና ከሶስት በላይ ተጫዋቾችን በማስመረጣቸው በውድድሩ ደንብ መሰረት ጨዋታ ለማድረግ አይገደዱም። በመሆኑም ጨዋታቸው ለሌላ ጊዜ ተላልፎ በተስተካካይ ጨዋታ እንዲያዝ መደረጉን የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አስታውቋል። በዚሁ መሰረት ጅማ አባጅፋር ከመከላከያ፣ ድሬዳዋ ከተማ ከደቡብ ፖሊስ፣ ወላይታ ድቻ ከሲዳማ ቡናና አዳማ ከተማ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ሊያደርጓቸው የነበሩ ጨዋታዎች ለሌላ ጊዜ መተላለፋቸውን ገልጿል። በሁለተኛ ሳምንት ባህርዳር ከተማና ስሑል ሽሬ የሚያደርጉት ጨዋታ የተራዘመ ሲሆን ጨዋታው የተራዘመበትን ምክንያት ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለማግኘት የተደረገው ጥረት አልተሳካም። ባለፈው የውድድር ዓመት በተወሰኑ ደጋፊዎች መካከል በተነሳ የስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል ምክንያት በ2010 ዓ.ም ጥር ጀምሮ በአማራና በትግራይ የሚገኙ ክለቦች ሲገናኙ በገለልተኛ ሜዳ እንዲጫወቱ ሲደረግ ቆይቷል። በትግራይና በአማራ ክልሎች የሚገኙ የእግር ኳስ ክለቦች ለጨዋታ ሲገናኙ በሜዳቸው እንዲጫወቱ ለማድረግ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን እየተሰራ ስለመሆኑ ፌዴሬሽኑ ከ11 ቀናት በፊት መግለጫ መስጠቱ ይታወሳል። ችግሩን ለመፍታት ከእግር ኳስ ፌዴሬሽን፣ ከስፖርት ኮሚሽንና ከሁለቱ ክልሎች ከተውጣጡ የተለያዩ አመራሮች ጋር ውይይት እንደተደረገ መሆኑንም አስታውቋል። እስካሁን በ2011 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች መቐለ ሰባ እንደርታና ኢትዮጵያ ቡና ሁለቱንም ጨዋታዎች በማሸነፍ 6 ነጥብ ይዘው ሊጉን በግብ ክፍያ ተበላልጠው እየመሩት ነው። በአንጻሩ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በሁለት ጨዋታ ተሸንፎ የሊጉ የመጨረሻ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም