ትኩረት የሚሻው  ቪዛ…

1540

ደሞዝ አያሌው/ኢዜአ/

ከፒያሳ ተነስቼ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል አካባቢ መድረሻዬን አደረኩ። ከታክሲ እንደወረድኩ ከገጠር  የሀገራችን አካባቢ  እንደመጡ እና ለአዲስ አበባ እንግዳ እንደሆኑ የሚያሳብቅባቸው በርከት ያሉ ወጣት ሴቶች አይኔ ውስጥ ገቡ። የኢሚግሬሽንና ዜግነት ጉዳይ  በራፍ ላይ ማለት ነው።

እኔም ወደ ወጣቶቹ ጎራ ብዬ የኢሚግሬሽንና ዜግነት ጉዳይ ፓስፖርት ለማውጣት የሚያስፈልጉ የተለያዩ ፎርሞችን ስታስጨርስ ያገኘኋትን ታደጊ ፋጡማ አብዩን ለምን እና እንዴት እንደመጣች እንድታወጋኝ ጠየኳት።

ታዳጊዋ በእኛ ምልከታ እንኳን ወደ ባእድ ሀገር ሄዳ እረፍት አልባውን ስራ ለመስራት ይቅርና  ከቤተሰብ ድጋፍ ተለይታ በሀገር ውስጥ ላለው ስራ እንኳን እንዳልደረሰች ለመገመት ቀላል ነው፡፡

ፋጢማ አብዩን ወዴት ሀገር ልትሄጂ ነው ? ብለን ላቀረብንላት ጥያቄ  ጂዳ  ነው በማለት  የገለጸችልን፡፡

ከኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ደራ ከሚባል ከተማ ከሀገር ውጭ ለመሄድ የሚያስፈልገውን ፓስፖርት ለማውጣት ወደ አዲስ አበባ  የመጣችው  ፋጢማ  ገና የ14 አመት ታዳጊ እንደሆነች ነው የተናገረችው።

እኛም ወደ አረብ ሀገር ለመሄድ የፈለገችበትን ምክንያትና ስላደረገችው ዝግጅት ፣ማን ሂደቱን እያስጨረሰላት እንደሚገኝ ጥያቄያችንን  አቀረብንላት።

የስምንተኛ ክፍል ተማሪ እንደነበረችና ትምህርቷን አቋርጣ ወደ አረብ ሀገር ለመሄድ እንደፈለገች የምትገልጸው ታዳጊዋ ጅዳ የት እንደሆነ እንኳን ወደማታውቀው ሀገር ያነሳሳትን አካል እንድትገልጽልን ላቀረብንላት ሀሳብ “እራሴ ፈልጌ ነው” ከማለት ውጪ  ማን እንደገፋፋት ለመናገር አልደፈረችም ፡፡

ታዳጊዋ ስለምትሰራው ስራም ሆነ የመግባቢያ ቋንቋ ምንም አይነት ግንዛቤም ሆነ የወሰደችው ስልጠና እንደሌለ ነው የተናገረችው፡፡

ፋጢማ ወደ ሳውዲ አረቢያ ጂዳ ከተማ ለመሄድ የሚያስፈልጉ የውጭ ጉዞ ሂደቶችን የሚያስጨርስላትን አካል እውነተኛ ማንነት ላለመናገር ፈራ ተባ እያለች  አባቴ  ነው በማለት የገለጸችልን፡፡

በኢትዮጵያ አንድ ሰው መታወቂያ ለመውሰድ 18 አመት ሊሞላው እንደሚገባ በህግ የተቀመጠ ቢሆንም ለ14 አመት ታዳጊ የመስጠት ጉዳይ ከህግ አንጻርም የሚያስጠይቅ በመሆኑ የሚመለከታቸው አካል መፍትሄ ሊሰጡት ይገባል እንላለን ፡፡

ከነበረችበት የሁለተኛ አመት የዩኒቨርሲቲ ትምህርቷን በጓደኞቿና በቤተሰብ ግፊት አቋርጣ ወደ ሳውዲ አረቢያ ሪያድ በደላላ አማካኝነት በመሄድ በ4 አመታት ቆይታ ለ16 ሰዓታት ያለመቋረጥ ስራ በመስራት “የአእምሮ ህምምተኛን በምንከባከብት ወቅት የመመታት እና  የጾታዊ ትንኮሳ  ሙከራ ተደርጎብኝ ነበር” በማት ያለፈ ታሪኳን የነገርችን ደግሞ ሌላዋ ወጣት ጠይባ ሀሰን ናት።

የደቡብ ወሎ ዞን አዳሜ ወረዳ ነዋሪ የሆነችው ወጣት ጣይባ  ከስደት ተመልሳ በሀገሯ የተለያዩ ሸቀጦች ንግድ ሥራ ላይ ተሰማርታ የራሷንና የቤተሰቦቿን ኑሮ እየመራች እንደሆነ ነው የነገረችን።

ስደት በነበርኩበት ወቅት ለመብቴ የሚቆም አካል ባለመኖሩ ችግሩን የከፋ አድጎት ነብር ያለችው  ጠይባ ˝የአረብ ሀገር ሴቶች ጠዋት ከቤት በሰላም ተሸኝተው  ከሰአት ስመለሱ በውሃ ቀጠነ ቁጣ በመጮህና በመማታት ሰራተኛ ላይ የሚያደርሱት በደል አስቸጋሪ ነው ˝ ብላለች፡፡

“በአስኮብላዮች የማማለያ ወሬ ተታለው በህገወጥ መንድ ወደ አረብ ሀገራት መሄድ ጉዳቱ የከፋ ሊሆን እንደሚችልና ለበርካታ ችግሮች የመዳረግ አጋጣሚው ሰፊ በመሆኑ ዜጎች ለጉዞ ባይመርጡት” በማለት መክራለች፡፡

በርካታ ዜጎች በህገወጥ መንገድ በባህር ላይ የሚያደርጉትን ስደት ለማስቆም የሚደረጉ ጥረቶች ፈታኝ ሆኖ ባለበት ሁኔታ፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የተለያዩ የቪዛ አይነቶችን በመጠቀም በኢትዮጵያ አየር መንገድ ዜጎች ህገ ወጥ  ጉዞን እያደረጉ ያለበት  ሂደትም  አሳሳቢ እየሆነ መምጣቱም ይነገራል።

ችግሩን ለመቅረፍ ከሚሰሩ አካለት ጋር የመከረው የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ከጥቅምት 26 /2011 ዓ.ም ጀምሮ በአየር መንገድ በኩል የሚደረግ ህገወጥ የሰዎች ዝውውር  መከልከሉንም ይፋ አድርጓል።

ህገወጥ በሆነ ቪዛ የኢትዮጵያ አየር መንገድን እንደ አማራጭ በመውሰድ በቀን ከ1ሺህ 300 በላይ ዜጎች ወደ ተለያዩ አረብ አገራት እንደሚጓዙ ሚኒስቴሩ ጠቅሷል  ፡፡

ለህክምና፣ ለጉብኝት፣ ለዘመድ ጥየቃና ንግድ ስራዎች የሚሰጡ ቪዛዎችን በህገወጥ መልኩ የሚወጡ ዜጎችን ለተለያዩ አደጋዎች ለሚያጋልጥ ዝውውር  ምክንያት መሆኑም ይጠቀሳል።

እነዚህ ሀገወጥ ደላሎች ለሌላ አላማዎች በተዘጋጀ ቪዛ እንዲጓጓዙ ሲያደርጉ ዜጎች ለእስር፣ ለአካል መጉደልና ለአእምሮ መታወክ፣ ለአስከፊ ህይወትና ለሞት እየተዳረጉ ከመሆኑም ባሻገር ህጋዊ ከለላ እንዳያገኙም ሆኗል ያሉት የሚኒስቴሩ  የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ አሰፋ ይርጋለም  ናቸው።

ወደ ውጭ ሀገራት ለሥራ ስምሪት መሄድ የሚፈልጉ ዜጎች፤ አስፈላጊውን መስፈርት በማሟላት በህጋዊ ኤጀንሲዎች ስልጠናዎችን በመውሰድ እና የሁለትዮሽ ስምምነት በተደረገባቸው ሀገራት ብቻ ሊሆን እንደሚገባው ይገለጻል። አሁን አሁን ግን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በህገወጥ ደላሎች  በመገፋፋት የሚሄዱ አካት  ጉዳይ  አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል፡፡

በተለይም ወደ የአረብ ሀገራት የሚደረጉ የዜጎች ጉዞ ላይ ሲከሰቱ የነበሩ የመብት ጥሰቶች፣ የአካል መጉደልና አልፎ አልፎ ሲደርሱ የነበሩ የህይወት ማጣት ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችሉ የህግ ማእቀፍም ከጥቂት ዓመት በፊት መዘጋጀቱም ይታወሳል ። መንግስት  በህገመንግስቱ የተቀመጠውን በነጻነት ተንቀሳቅሶ የመስራት መብት ውጤታማ ለማድርግ፣ የዜጎችን ተጠቃሚነትና መብት ለማስከበር የሚያስችል የሁለትዮሽ  ስምምነትም ከ3 ሀገራት  ጋር ተፈርሟል። ለዜጎች ህጋዊ የስራ ስምሪት የሁለትዮሽ ስምምነት የተደረሰባቸው አገራት ሳዑዲ አረቢያ፣ ኳታርና ጆርዳን ብቻ መሆናቸውም  ይፋ ተደርጓል፡፡

በስምምነቱ ውስጥ ከተቀመጡ ነጥቦች ዜጎች ወደ ሀገራቱ በሚያደርጉት የስራ ጉዞ አስቀድሞ በብቃት ምዘና ሰርተፍኬት የተረጋገጠ በቂ ስልጠናና የስነልቦና ስንቅ  መያዝ እንደሚያስፈልግ ይገልጻል፡፡

ከተጠቀሱት የመካከለኛው ምሥራቅ ሃገራት ውጪ በተለያዩ መንገዶች ለሥራ መጓዝ ህገወጥ እንደሆነ፤ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ቁጥጥር እንደሚያደርጉና  እርምጃ እንደሚወስዱም  በተደጋጋሚ ስገለጽ ይሰማል።

ይህ ሆኖ ሳለ ግን “እኔ ከሞትኩ …” እንደሚሉት አበው ህገወጥ አዘዋዋሪዎች የተለያዩ የቪዛ አይነቶችን እንደሽፋን በመጠቀም ወደ ተለያዩ ሀገራት የሚደረጉ ህገወጥ የዜጎችን ዝውውር እየሰፋ መጥቷል። እነዚህን ችግሮች ለመግታት መንግስትና እያንዳንዱ ዜጋ  የድርሻውን ሊወጣ ይገባል እንላለን።

ቸር እንሰንብት!