በትራንስፖርት አገልግሎት ዘርፍ ለመሰማራት የወጡ መስፈርቶችን መከተል ግዴታ ነው ተባለ

66
አዲስ አበባ ጥቅምት 27/2011 የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት ባለስልጣን በትራንስፖርት አገልግሎት ዘርፍ ለመሰማራት የባለስልጣኑን መስፈርት መከተል ግዴታ መሆኑን አስታወቀ። የባለስልጣኑ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ዳዊት ዘለቀ በሰጡት መግለጫ  በአዲስ አበባ ከተማ ህጋዊ ያልሆኑ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ማህበራት ይገኛሉ። ማህበራቱ የባለስልጣኑን መስፈርቶች እንዲያሟሉና ህጋዊ እንዲሆኑ ቢነገራቸውም ሊያስተካክሉ ባለመቻላቸው አገልግሎታቸው እንዲታገድ መወሰኑን አስታውቀዋል። የተሽከርካሪውን አይነት ማስመዝገብና በአክሲዮን ማህበራት ተደራጅቶ መምጣት ብቻውን በህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ዘርፍ ለመሰማራት በቂ እንዳልሆነ የጠቀሱት ዋና ስራ አስኪያጁ የሚሰጠው አገልግሎት በቴክኖሎጂ መታገዝ እንዳለበት ተናግረዋል። መንግስት የብዙሀን ትራንስፖርት አውቶቡሶችን ቁጥር በመጨመር የከተማዋን የትራንስፖርት ችግር ለመቀነስ እየሰራ መሆኑን ገልጸው በ2011 ዓ.ም ግዙፍ የመንገድ መሰረተ ልማት ለማከናወን መታቀዱንም አስረድተዋል። ለሚሰራው የመንገድ መሰረተ ልማት የሚመጥን የብዙንሀን ትራንስፖርት አገልግሎት እንዲኖርም እቅድ መያዙን ጠቁመዋል። ለሚገነባው መሰረተ ልማትና ቁጥራቸው ለሚጨምረው የብዙሀን ትራንስፖርት ተሽከርካሪዎች የሚመጥን ተደራሽና ዘመናዊ የአሰራር መዋቅር እንዲኖር ማድረግም የእቅዱ አንድ አካል መሆኑ ተነግሯል። የከተማዋ የትራንስፖርት አገልግሎት የብዙሀን ትራንስፖርት ሰጭ አውቶብሶች የበዙበት እንዲሆን ማድረግ ቢሆንም ህጉን አክብረው የሚመጡ አካላት በአነስተኛና መለስተኛ አገልግሎት ሰጭ ተሽከርካሪዎች ዘርፍ ላይም መሰማራት እንደሚችሉ ባለስልጣኑ አመልክቷል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም