ኑሯችንን ቀላል እናድርግበት!

1354

አስቴር ታደስ /ኢዜአ/

የሰው ልጅ አእምሮ በየጊዜው የሚያፈልቃቸው አዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ሊገጥሙት የሚችሉትን የህይወት ሳንካዎች  ከመቀነስ ባሻገር የእለት ተእለት ኑሮውን እያቀለሉለት ይገኛል። እድገቱ፣ ስፋቱና ምጥቀቱ አሁንም ድረስ ያለማቋረጥ እየፈለቀ ያለው ቴክኖሎጂው ጊዜና ኃብትን በመቆጠብ አድገትን በማጎናጸፍ ረገድ እየተጫወተ ያለው ሚና የትየለሌ ነው።

ከነዚህ የቴክኖሎጂ ውጤቶች መካከል አንዱና ምናልባትም ዋነኛው የምንኖርበትን እጅግ ሰፊ ዓለም ከአፅናፍ አፅናፍ በማገናኘት አንዲት ትንሽዬ መንደር አስክትመስል ያቀራረበው ኢንተርኔት ነው። በመላው ዓለም በየሰከንዱ አየሆነ ያለውን ክስተት በቅርበት ለመከታተልና ለማወቅ ከማስቻል አልፎ የሰው ልጅ የሚሻውን ነገር ሁሉ እየሆነ መጥቷል- ኢንተርኔት።

በዚህም የተነሳ ዓለም ስለሚሻው ብቻ ሳይሆን የግድ ስለሆነበት ጭምር የዚህ ቴክኖሎጂ ጥገኛ የሆነበት ደረጃ ላይ ተደርሷል። ይህ ቴክኖሎጂ አዋጭ ብቻ ሳይሆን የግድ እሆነበት ደረጃ እየደረሰ በመምጣቱም የተጠቃሚው ቁጥር ከእለት ወደእለት እየጨመረ ይገኛል። ባለፈው የአውሮፓ ዓመት ይፋ በሆነው መረጃ መሰረት እንኳ በመላው ዓለም አራት ቢሊዮን የሚጠጋ ህዝብ የኢንተርኔት ተጠቃሚ ነው።

በአሁኑ ወቅት በተለይ በኢንዱስትሪ በበለፀጉት አገራት ካለው የስራ ጫናና የጊዜ እጥረት አኳያ ይህ ቴክኖሎጂ እየሰጠ ያለው በረከት ተነግሮ የሚያልቅ አይመስልም። በእነዚሀ ዓለማት አሁን አሁን የህክምና ቀጠሮ ወረፋ መያዝን፣ አልባሳት መረጣና ግዥን፣ አስቤዛ ሸመታንና የሚሿቸውን ሌሎች አገልግሎት ሁሉ  እጃቸው ላይ ባለው ተንቀሳቃሽ ስልክ አማካኝነት ባለው የኢንተርኔት መስተጋብር ብቻ በመጠቀም መፈጸም የተለመደ ተግባራቸው ከሆነ ቆየ።

ቴክኖሎጂውን በከፍተኛ መጠን እየተጠቀሙበት ካሉት የዓለማችን አገራት ህዝቦች መካከል ደግሞ አንዷ ቻይና ናት። በሕዝብ ብዛቷ በዓለም ግንባር ቀደም በሆነችው በዚህች አገር ያለው የኢንተርኔት ቴክኖሎጂ አገልግሎት አስደማሚ ስለመሆኑ በአገሪቱ በነበረኝ የአራት ሳምንታት ቆይታ ተገንዝቤያለሁ። ከ1 ነጥብ 4 ቢሊዮን በላይ ከሚልቀው ህዝቧ ከ60 በመቶ በላዩ የኢንተርኔት ተጠቃሚ ነው።

ቻይናውያን ሁሉንም ተግባራቸውን የሚከውኑት በእጅ ስልካቸው ላይ ባለ የኢንተርኔት አገልግሎት ነው። ክፍያ የሚፈጽሙት፣ ታክሲና አውቶብስን የመሳሰሉ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚያገኙትና ክፍያ የሚፈፅሙት፣ የሚሹትን አልባሳትንና ምግባቸውን ከገበያ አስካሉበት ቦታ ድረስ የሚያስመጡትም ሆነ የአውሮፕላንና የባቡር ትኬት ጨምሮ ሌሎች ለእለት ተእለት ኑሮአቸው የሚያስፈልግ ቁሳቁስን የሚሸምቱት በዚሁ እጃቸው ላይ በማትጠፋው የተንቀሳቃሽ ስልካቸው አማካኝነት በቀረበላቸው ኢንተርኔት አገልግሎት ነው።

በቻይና ጥሬ ገንዘብ ይዘው የሚንቀሳቀሱ በጣም ጥቂቶች ሲሆኑ አብዛኛዎቹ የኢንተርኔት አገልግሎቱን የማይጠቀሙት በእድሜ የገፉ አዛውንቶች ብቻ ናቸው።

በጣም አስገራሚው ነገር ደግሞ በየከተማውና በየአቅራቢያው በርካታ የባንክ አገልግሎቶች የሚሰጡ ቅርንጫፎች ቢኖሩም በባንኮቹ ጥሬ ገንዘብ የሚያንቀሳቅስ ሰው ለማግኝት በርካታ ሰአትን ቁጭ ብሎ መጠበቅ ያስፈልጋል፡፡ ይህች አገር ከአለም ትልቁ የሰው ሃብት ያላት፣ ለሕዝቦቿ ፈጣን እድገት በማምጣት ድህነትን እያሸነፈች ያለች ለመሆን የበቃችው ይህንን ዘርፍ በአግባቡ በመጠቀሟ ጭምር መሆኑን መገመት አያዳግትም።

በቻይናውያን ዘንድ እንደፌስቡክ ዓይነቱ የምእራባውያን ስሪት የሆነ ማህበራዊ ሚዲያ አይታወቅም። በእነርሱ ዘንድ በስፋት የሚታወቀው ማህበራዊ ሚዲያ አገር በቀል የሆነው ”ዊ ቻት” ነው። የቻይናዊያኑ ”ዊ ቻት” እኛንና እኛን በመሰሉ የአፍሪካና ሌሎች አገራት በስፋት ጥቅም ላይ የሚውለውን ፌስ ቡክ የተካ ገፅ ነው። ታዲያ እያንዳንዱ ሰው የዚህ ማህበራዊ ትስስር ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ መሆን የሚችለው በትክክለኛ ስምና አድራሽ ብቻ ነው።

አድራሻው ህጋዊ ከሆነ የስልክ ቁጥር ጋር የሚቆራኝ በመሆኑ ማንም ትክክለኛ የሆነ ስሙንና አድራሻውን ማስመዝገብ ካልቻለ ተጠቃሚ መሆን አይችልም። ይህ የአሰራር ስርዓት ብቻ ሳይሆን በአገሪቱ ሕግ ጭምር የተደነገገ ነው። በመሆኑም በቻይና ማህበራዊ ሚዲያ መስተጋብር ውስጥ በሀሰት ስምና አድራሻ የሚወጣ ገፅ አይገኝም።

”ዊ ቻት” ድምፅና ምስልን ጨምሮ የተለያዩ ዘርፈ ብዙ (መልቲሚዲያ) የሚዲያ አገልግሎቶችን የሚሰጥ ከመሆኑም በላይ የባንክ አገልግሎትም ያገኙበታል።

ወደኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ስንመጣ ደግሞ በአሁኑ ወቅት 15 ሚሊዮን ያህል ኢንተርኔት ተጠቃሚዎች እንዳሉ በቅርቡ የወጣ መረጃ ያመለክታል፡፡

ከዚሁ ከኢንተርኔት ተጠቃሚ ሕዝብ ውስጥ በአብዛኛው የማሕበራዊ ሚዲያ በተለይም የፌስ ቡክ ተጠቃሚ ነው ተብሎም ይታመናል፡፡ በተለይም በአዲስ አበባ በአብላጫው ወጣቱና የተማረው የህብረተሰብ ክፍል የፌስ ቡክ ማሕበራዊ ሚዲያ ንቁ ተሳታፊ እንደሆነ ይነገራል። ቴክኖሎጂው በተለይ መረጃ ለመለዋወጥ ዓይነተኛ ሚና እየተጫወተ መሆኑ እሙን ቢሆንም በወጉ ጥቅም ላይ እየዋለ ነው ለማለት ግን ያዳግታል።

በአገራችን ይህ የማህበራዊ ሚዲያ መልካም ማህበራዊ ግንኙነት ማጠናከሪያና የእለት ተእለት ኑሮን ማቅለያ መሆን ሲገባው አላስፈላጊ በሆኑና  በማህበረሰቡ መካከል ቅራኔን በሚፈጥሩ፣ የወጣቱን መልካም አስተዳደግና ስነ-ምግባር የሚያቆሽሹ ተግባራት የሚፈፀሙበት መድረክ ሆኖ ይታያል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ በዜጎች መካከል ጥርጣሬ እንዲፈጠር፣ የአገሪቱ የፖለቲካ ሁኔታ አንዳይረጋጋ፣ ሰላምና ደህንነት እንዲጠፋ በአጠቃላይ በህዝቡ ውስጥ ስጋት እንዲነግስ የሚያደርጉ የተሳሳቱ መረጃዎችና ውዥንብር የሚነዛበት አውታር እየሆነ ይገኛል። ፡

ይህንን በዋነኝነት የሚፈፅሙት ደግሞ መጥፎ ግብ ያነገቡና በሀሰተኛ ስምና አድራሻ የፌስ ቡክ ገፅ የሚጠቀሙ አካላት ናቸው። አያሌ መልካም ትሩፋቶች ሊሰጠን የሚችለውን ይህንን ቴክኖሎጂ አግባብ ባልሆነ መንገድ ጥቅም ላይ መዋሉ የአያሌዎች መልካም ስብእና በሀሰት ጎድፏል፣ በየአካባቢው ለተፈጠረው አለመግባባት፣ ግጭት፣ የሰው ህይወት መጥፋትና መፈናቀል የበኩሉን ሚና ተጫውቷል።

እነዚህ አካላት ከሰዓት በፊት የአንዱ ብሔር  ደጋፊ፤ ከሰአት በኋላ ደግሞ የሌላው ብሔር ተቆርቋሪ በመሆን በመካከሉ የማይገባ ጥላቻና መጠራጠር እንዲነግስ ብሎም ግጭት ውስጥ እንዲገባ በሚያደርጉ ተግባራት ተጠምደው ይታያሉ።

እንደኔ እንደ እኔ በተለይ የፌስ ቡክ አገልግሎት ከአገር ሰላምና ከሕዝብ ደሕንነት የማይበልጥ በመሆኑ ሀግና ስርአት ሊበጅለት የሚገባ ነው እላለሁ።

በመሆኑም ይህ አገልግሎት ማንም እንደፈለገ የሚፈነጭበት፣ አገርንና ህዝብን ለጥፋት የሚዳርግ ዓላማ የሚያስፈፅምበት እንዲሆን መፍቀድ አይገባም። በመሆኑም በእድገቷ ዓለምን እያስደመመች ካለችው ቻይና ልምድ መውሰድ ይገባል። የአገራችን የማህበራዊ ሚዲያ በተለይም የፌስ ቡክ አጠቃቀም ለአገርና ዜጎች ሰላምና እድገት የሚበጅ፣ የዜጎችን እውነተኛ የሀሳብ  ነፃነት የመግለፅ መብት የሚያስከብር፣ ህገ-ወጥነትን ለመከላከል የሚያስችል ሆኖ ህግና ስርዓት ሊበጅለት ይገባል።

መንግስት ይህንን ዘርፍ ህግና ስርዓት ለማስያዝ የጀመረውን ጥረት ሊያፈጥነው ይገባል።  የሚወሰደውን ስርዓት የማስያዝ ተግባር “ሀሳብን በነፃነት ከመግለፅ መብት” ጋር በማያያዝ ሊነቅፉ ለሚሹ አካላት ጆሮ መስጠት የሚገባ አይመስለኝም። ይህ ጉዳይ የብሄራዊ ደህንነት ጉዳይ ነው፤ ይህ ጉዳይ በሚሊዮን የሚቆጠረው ድሃ ኢትዮጵያዊ የወደፊት ህልውና ተደርጎ መወሰድ አለበት።

ጉዳዩ አሁን ባለበት መልኩ በዝምታ የሚታለፍ ከሆነ በአጭር ጊዜ ውስጥ በአገርና ህዝብ ላይ የሚደርሰው ጥፋት የከፍ እንደሚሆን መገመት አያዳግትም። በመሆኑም በኢትዮጵያ ከማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ጋር በተያያዘ ያለው ጉዳይ ከምንም ነገር በላይ ከፍ ብሎ ሊታይ የሚገባው የብሄራዊ ደህንነት ጉዳይ ነው። የሚወጣው ህግም ይህንን መሰረት በማድረግና የአገሪቱን ተጨባጭ እውነታ ያገናዘበ እንዲሆን ሁሉም የሚሻ ይመስለኛል።

የማሕበራዊ ሚዲያ ህግና የአሰራር ስርዓቱ ለአገር ጥቅምና እድገት በተሻለ መልኩ የምንጠቀምበትን መንገድ የሚዘይድ፤ ኑሯችንን የምናቀልበት እንዲሆን የሚያግዘንን አቅጣጫ ያመላክተናል የሚል እምነትና ተስፋ አለኝ። የዚህን የቴክኖሎጂ ትሩፋት አደጋ በመግታት ኑሯችንን በምናቀልበት መንገድ ብንጠቀምበትስ።

ሰላም ሁኑ