ብሔራዊ የሩዝ ምርምርና ሥልጠና ማዕከል ወደ ስራ ይገባል

160
አዲስ አበባ  ጥቅምት 27/2011 የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲቲዩት በጃፓን አለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ (ጃይካ) ትብብር ያሰራውን ብሔራዊ የሩዝ ምርምርና ሥልጠና ማዕከል በመጪው ቅዳሜ በይፋ ይከፍታል። ማዕከሉ በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ከባህር ዳር በ60 ኪሎ ሜትር ርቀት በፎገራ ወረዳ ይገኛል። ማዕከሉ የተቋቋመው በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲቲዩት ሲሆን ለምርምር ሥራው የሚያስፈልጉ የመሰረተ ልማት ሥራዎች የተሟሉት በጃይካ ድጋፍ ነው። የሩዝ ምርት ለግብርና ትራንስፎርሜሽን አጀንዳ ከፍተኛ አስተዋፆ ያለው መሆኑን የፖሊሲ አውጪዎች እና የልማት አጋሮችን ትኩረት ስቧል። እ.አ.አ. በ2016 ወደ አገር ውስጥ ለገባ የሩዝ ምርት 200 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ወጪ ተደርጓል። የማዕከላዊ ስታቲክስ ኤጀንሲ መረጃ እንደሚያመላክተው ለሩዝ ምርት ተብሎ የሚዘጋጅ የመሬት አቅርቦት እየጨመረ መሆኑንና በዚህም በ2016 ብቻ 46ሺህ ሄክታር የሚጠጋ መሬት ለሩዝ ምርት ተብሎ የተዘጋጀ እና 134ሺ አርሶ አደሮችን ያካተተ ነበር። ይሁን እንጂ ለሩዝ ምርት ያለው የመሬት አቅርቦት እየጨመረ ቢሄድም ከምርታማነት አኳያ ግን ዝቅተኛ ነበር። በመሆኑም አሁን የተቋቋመውና በመጪው ቅዳሜ የሚከፈተው ብሄራዊ የሩዝ ምርምርና ሥልጠና ማዕከል በሩዝ ምርትና አይነቶች ላይ ምርምር በማድረግ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ረገድ ከፍተኛ አስተዋፆ ይኖረዋል ተብሏል። የሩዝ ኢንዱስትሪው ከሚያስገኛቸው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች መካከል ሩዝና ጤፍን በማቀናጀት እንጀራ የሚጋገርበትን ዘዴ ማመቻቸትና ገበሬዎች በኢኮኖሚ ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ሁኔታዎች ማመቻቸት መሆኑንም ተጠቁሟል።            
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም