እንቦጭን የማስወገድ ሥራ ለእንስሶቻቸው የመጠጥ ውሃ እየጠቀመ መሆኑን አርሶ አደሮች ገለጹ

117
ባህር ዳር ሚያዝያ 23/2010 በጣና ሐይቅ ላይ የተከሰተውን የእንቦጭ አረም ለማስወገድ እየተደረገ ያለው ጥረት በሐይቁ ዳር ተዘግቶ የነበረውን የእንስሳት ውሃ መጠጫ ቦታ በመክፈቱ ተጠቃሚ እያደረጋቸው መሆኑን አርሶአደሮች ገለጹ። በሐይቁ ላይ የተከሰተውን የእንቦጭ አረም በሰው ጉልበትና በዘመናዊ ማሽን በመታገዝ የስርጭት መጠኑን ለመቀነስ ጥረቱ ተጠናክሮ እንደቀጠለ ነው። የዳሽን ባንክ ሠራተኞች የእንቦጭ አረሙን ከሐይቁ ከማስወገድ ባለፈ ሥራውን በገንዘብ ለመደገፍም ዝግጁ መሆናቸውንም ተናግረዋል። በጎንደር ዙሪያ ወረዳ የሸሃ ጎመንጌ ነዋሪ አርሶ አደር ጠጋው ጌታሁን ለኢዜአ እንደገለጹት የእምቦጭ አረም ከመጣ ወዲህ በሐይቁ በብዛት ይገኝ የነበረው የዓሣ ሃብት እየቀነሰ መጥቷል። የእምቦጭ አረሙ የሐይቁን ዳርቻ በመውረሩ የተነሳ እንስሳት በሐይቁ ዳር ውሃ ለመጠጣትም ሆነ የአሳ ማስገሪያ ታንኳና የሞተር ጀልባ እንደልብ ወጥቶ ለመግባት በር በመዘጋቱ ተቸግረው እንደነበር አስታውሰዋል። የእምቦጭ አረሙን ሕብረተሰቡ በጉልበቱ ለማስወገድ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን የገለጹት አርሶ አደር ጠጋው፣ አረሙ በፍጥነት መልሶ በመውረር ልፋታቸውን ከንቱ እያደረገባቸው መሆኑን ተናግረዋል። ለአረሙ ማስወገጃ ማሽን መጥቶ ሥራ መጀመሩ የጉልበታቸውን ድካም ከመቀነሱ በላይ በሐይቁ ዳርቻ ተወሮ የነበረውን አረም በማስወገድ እንስሳት ያለምንም ችግር ከሐይቁ ውሃ እንዲጠጡ ያስቻላቸው መሆኑን ተናግረዋል። የእንቦጭ አረሙ በሐይቁ ዳር የእንስሳት የግጦሽ ቦታውን በመውረር "ቶካ" ተብሎ ይጠራ የነበረውን የእንስሳት መኖ ሳር ሙሉ በሙሉ በማውደም እንስሳትን ለመኖ እጥረት መዳረጉን የገለጹት ደግሞ አርሶ አደር እሸቴ አድማስ ናቸው። እንስሳቱ በቂ ምግብ ካለማገኘታቸው የተነሳ የእንቦጭ ተክሉን በመመገብ ላይ መሆናቸውን ገልጸው፣ በእዚህም ሰውነታቸው ከመክሳቱ ባለፈ ለበሽታና ለሞት እየተጋለጡ መሆናቸውን አመልክተዋል። የዳሽን ባንክ የባህር ዳር ዲስትሪክት ሥራ አስኪያጅ አቶ እሸቴ የማታ በበኩላቸው፣ አረሙን በቴሌቪዥንና በአካል ሲመለከቱት የጎላ ልዩነት እንዳለው ማስተዋላቸውን ተናግረዋል። በአሁኑ ወቅት አረሙ በሐይቁ ላይ ጉዳት እያደረሰ ስለመሆኑ በአካል ማየታቸው ከፍተኛ ቁጭት እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል። ባንኩ ከመደበኛ ሥራው ጎን ለጎን በማህበራዊ አገልግሎት በመሳተፍ ቀደም ሲል 2 ሚሊዮን ብር ለእንቦጭ አረም ማስወገጃ የሚውል ብር መለገሱን አስታውሰው፣ "በቀጣይም ሠራተኛውን በማስተባበርና የችግሩን ስፋት በማሳየት ድጋፉ ለማስቀጠል ጥረት ይደረጋል" ብለዋል። በአማራ ክልል አካባቢ፣ ደንና ዱር እንስሳት ባለስልጣን የእምቦጭ መከላከል ህብረተሰብ ግንዛቤ ፈጠራ ባለሙያ አቶ ቻላቸው ብናልፈው በበኩላቸው የእምቦጭ አረም አሁንም ለሐይቁ ስጋት መሆኑን ገልጸዋል። በዚህ ዓመት መጀመሪያ በተካሄደ ልኬት 5 ሺህ 400 ሄክታር የሚጠጋ የሐይቁ አካል በአረሙ መወረሩንና ይህንን ለማስወገድ ሕብረተሰቡ ባደረገው ጥረት 80 በመቶ ማስወገድ መቻሉን አመልክተዋል። የአርሶ አሩን ድካም ለመቀነስ በማሽን የታገዘ የማስወገድ ሥራ መጀመሩን ጠቁመው፣ በቀጣይም ሌሎች ማሽኖችን ለማስገባት በሂደት ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል። በማሽኑም ሆነ በሕብረተሰቡ የሚወገደው የእምቦጭ አረም ሌለ ቦታ ተጓጉዞ የሚቃጠል ባለመሆኑ በሐይቁ ዳርቻ መልሶ እየተስፋፋ መሆኑን ገልፀዋል። አረሙን ሌላ ቦታ አጓጉዞ ለማስወገድ የማቃጠያ ቦታዎች መመረጣቸውንና ለማጓጓዣየሚሆን የመንገድ ግንባታ እየተከናወነ መሆኑንም አብራርተዋል። የእምቦጭ አረም በጣና ሐይቅ ላይ ከስድስት ዓመት በፊት መከሰቱ ይታወሳል ነው።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም