በኢትዮጵያ የተጀመረው የአንድነት ጉዞ እንዲሳካ የክልሎች ሚና ወሳኝ ነው ፤-የድሬዳዋ አስተዳደር አፈ ጉባዔ

80
ድሬዳዋ ጥቅምት 27/2011 በኢትዮጵያም ሆነ በአፍሪካ ቀንድ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍንና የተጀመረው የአንድነት ጉዞ እንዲሳካ የምሥራቅ አጎራባች ክልሎች የተቀናጀ ርብርብ ወሳኝ መሆኑን የድሬዳዋ አስተዳደር አፈ ጉባዔ አብዱልሰላም መሐመድ ተናገሩ፡፡ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሂምን ጨምሮ የምሥራቅ ተጎራባች ክልሎች ከፍተኛ አመራሮች የሚሳተፉበት የሰላም ጉባዔ በድሬዳዋ ከተማ ከነገ ጀምሮ ለሁለት ቀናት ይካሄዳል፡፡ አፈ ጉባዔው እንደተናገሩት በአገሪቱ የተጀመረው ለውጥና  አገር ግንባታ እንዲሳካ የምክር ቤቱ አባላት፣ በየደረጃው የሚገኘው አመራር፣ ባለሙያዎችና ነዋሪዎች ኃላፊነት አለባቸው፡፡ የምስራቅ  ኢትዮጵያና አጎራባች ክልሎች ለዘመናት ያዳበሩትን የፍቅር፣ የመቻቻልና የአንድነት ባህላዊ እሴቶች በማጠናከር ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ ተቀናጅተው መስራት እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡ ጉባዔው የምሥራቅ ኢትዮጵያ አጎራባች ክልሎች በተቀናጀ መንገድ በአገሪቱ ብሎም በአፍሪካ ቀንድ ሀገሮች ሰላምና ልማት እንዲረጋገጥ የተጀመሩትን ተግባራት ለማሳካትም አበርክቶው የጎላ እንደሚሆን አቶ  አብዱልሰላም አመልክተዋል፡፡ ለጉባዔው የሚያስፈልጉ የመስተንግዶ፣የመሰብሰቢያ አዳራሾች፣የእርስ በርስ ባህላዊ እሴቶችና የልምድ ልውውጥ መከወኛ ሥፍራዎች ተዘጋጅተዋል። የድሬዳዋ ከተማ ነዋሪዎችና አገልግሎት ሰጪ  ተቋማት እንግዶችን በፍቅርና በደስታ በማድተናገድ ከተማዋ የፍቅር ተምሳሌት መሆኗን  በተግባር እንዲያስመሰክሩ አፈ ጉባዔው ጥሪ አቅርበዋል። በጉባዔው የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሂምን ጨምሮ የምስራቅ አጎራባች ክልሎች ርዕሳነ መስተዳድር፣ አፈ ጉባዔዎች፣ ከንቲባዎች፣ የአገር ሽማግሌዎች ወጣቶችና ሴቶች ይሳተፋሉ ብለዋል፡፡ የዘንድሮውን  የብሄሮች፣ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ቀን አስመልከቶ ነገ በምሥራቁ የአገሪቱ ክፍል ድሬዳዋ ላይ የሚጀመረው የሰላምና የአንድነት ጉባዔ በቀጣይም በምዕራብ፣በደቡብና በሰሜን የአገራቸን ክፍሎች እንደሚቀጥል መረጃዎች ያመለክታሉ።              
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም