በኢትዮጵያ 25 ሚሊዮን ዜጋን በጤናና አካል ብቃት ለማሳተፍ የተያዘው እቅድ አልተሳካም

79
አዲስ አበባ ጥቅምት 27/2011 በኢትዮጵያ በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ 25 ሚሊዮን ህዝብን በጤናና አካል ብቃት እንቅስቃሴ ለማሳተፍ   የነበረው ውጥን  ማሳካት አልተቻለም ተባለ። በአስካሁኑ የእቅዱ ትግበራ በጤናና አካል ብቃት እንቅስቃሴ ማሳተፍ የተቻለው 1 ሚሊዮን ዘጠኝ መቶ ያህል ህዝብን ብቻ ነው። የማህበረሰብ የጤናና አካል ብቃት  ስፖርቶች ተብለው ከሚጠቀሱት መካከል ኤሮቢክስ፣ ዳንስ፣ ፈጣን የእግር ጉዞ፣ ገመድ ዝላይ፣ ደረጃ መውጣትና መውረድና ሌሎች መሰል እንቅስቃሴዎች ይገኙበታል። እነዚህን የመሳሰሉ የጤናና አካል ብቃት እንቅስቃሴ አለማድረግ ሲጋራ ከማጤስ የበለጠ ለልብ ህመምና በሽታ የሚያጋልጥ መሆኑን በቅርቡ በአሜሪካው ታይምስ መጽሄት ላይ የወጣ አንድ ጥናት አመልክቷል። አካላዊ እንቅስቃሴ አለማደረግ ሰዎችን አላስፈላጊ ለሆነ ውፍረት በመዳረግ እንደ ስኳር፣ ደም ግፊትና ሌሎች ተላላፊ ያልሆኑ ገዳይ በሽታዎች ያጋልጣል። ባለፈው መስከረም ወር በዓለም አቀፉ ጤና ድርጅት ይፋ የሆነ መረጃ እንደሚያመላከትው ከዓለም ህዝብ 1 ነጥብ 4 ቢሊዮን ወይም ከአራት ስዎች አንዱ የጤናና አካል ብቃት እንቅስቀቃሴ እንደማያደርግ አስታውቋል። በኢትዮጵያም የአካል እንቅስቃሴ በብዙዎች ዘንድ የማይዘወተር መሆኑ ይነገራል። በዚህም የተነሳ በኢትዮጵያ ብዙም የማይታወቁ የነበሩት ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች በአሁኑ ወቅት በአሳሳቢ ደረጃ እየተስፋፉ መምጣታቸውን የህክምና ባለሙያዎች በተደጋጋሚ ሲገልፁ ይደመጣሉ። ለዚህም ከሚጠቅሷቸው ምክንያቶች መካከል ዋነኛው የአካል ብቃል እንቅስቃሴ ባህል ዝቅተኝነትና የአመጋገብ ዘይቤ ኋላቀርነትን ናቸው። ኢትዮጵያ ይህን ችግር ለመከላከል በሁለተኛው እቅድና ትራስፎርሜሽን እቅድ ዘመን 25 ሚሊዮን የሚሆነውን ህዝብ የጤናና አካል ብቃት እንቅስቃሴ አዘውታሪ ይሆን ዘንድ ለመስራት አቅዳ ነበር። ይሁንና የእቅዱ ዘመን ሊጠናቀቅ ሁለት ዓመት ብቻ የቀረው ቢሆንም  እስካሁን 1 ሚሊዮን 900 ሰዎችን ብቻ ነው ማሳተፍ የተቻለው። በስፖርት ኮሚሽን የስፖርት ውድድርና ተሳትፎ ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ በቀለ መርሃግብሩ በ2008 ዓ.ም ከ1 ሺህ 300 በላይ ለሚሆኑ አሰልጣኞች ስልጠና በመስጠት የተጀመረ ቢሆንም በተግባሩ ጥቂት ጅማሮዎች ብቻ እንዳሉ ነው የገለጹት። በሀገር አቀፍ ደረጃ ስኬታማ የሚባል ባይሆንም በንጽጽር የተሻሉ ስራዎች ያሉት ግን በአማራ ክልል የተወሰኑ ቦታዎች ብቻ ነው ብለዋል። በደቡብ ክልል ሶስት ዞኖች፣ በኦሮሚያና አንዳንድ ከተሞችና በአዲስ አበባ በተወሰኑ ትምህርት ቤቶች የተጀመሩ ጥረቶች ያሉ ቢሆንም እቅዱን ማሳካት ግን እንደተሳናቸው አመልክተዋል።  ለዚህም ዋነኛ የሚባሉት ችግሮች የአመራር ድክመትና የበጀት እጥረት ሲሆኑ እየተከናወኑ ያሉት ተግባራትም ቢሆኑ ወጥነት የሌላቸው ናቸው ብለዋል። ወደፊት ስፖርታዊ እንቅስቃሴውን ለማስፋፋት የእግር ጉዞን ጨምሮ የተለያዩ ስፖርታዊ ኩነቶችን ለማከናወን የታቀደ መሆኑን አመልክተዋል። አንዳንድ የመንግስት መስሪያ ቤቶችም ጂም ቤቶችን እያሰሩ ያሉ እንዳሉ አንስተዋል። ከእነዚህ መካከል ለአብነት ያነሱት  የትምህርት ሚኒስቴርን ሲሆን  በአራት ሚሊዮን ብር ወጪ የአካል ብቃት እንቅስቃሴ የሚሰራበት ቦታ አዘጋጅቷል።        
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም