ለሰላማዊ የመማር ማስተማር ስራ የበኩላችንን እንወጣለን - የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች

58
ጎንደር ጥቅምት 27/2011 ለሰላማዊ የመማር ማስተማር ስራ የበኩላቸውን እንደሚወጡ  የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ተናገሩ፡፡ የዩኒቨርሲቲው አመራሮች፣ መምህራንና ሰራተኞች ለነባር ተማሪዎች ዛሬ በቅጥር ግቢአቸው ደማቅ አቀባበል አድርገዋል፡፡ ከጋምቤላ ክልል የመጣውና በዩኒቨርሲቲው የ2ኛ አመት የቋንቋና ስነጽሁፍ ትምህርት ክፍል ተማሪ ኡቦንግ ኡመድ ሰላም የሁሉም መሰረት በመሆኑ ለሰላማዊ የመማር ማስተማር ስራ ተገቢውን ትኩረት እንደሚሰጥ ተናግሯል፡፡ ''ወላጆቼ ለከፍተኛ ትምህርት እንድበቃ ላለፉት 12 አመታት ከፍተኛ ድጋፍ አድርገውልኛል'' ያለው ደግሞ ከኦሮሚያ ክልል የመጣውና በዩኒቨርሲቲው የ2ኛ አመት የኢኮኖሚክስ ተማሪ ጫላ ታዬ ነው፡፡ ''የወላጆቼ ልፋትና ድካም ፍሬ አፍርቶ ለውጤት እንድበቃ ጠንክሬ ትምህርቴን ለመከታተል ወስኜ በመምጣቴ በዩኒቨርሲቲ ቆይታዬ ለሰላማዊ የመማር ማስተማር ስራ ስኬታማነት የበኩሌን ጥረት አደርጋለሁ'' ብሏል፡፡ ከትግራይ ክልል ዳንሻ አካባቢ የመጣውና በዩኒቨርሲቲው የ2ኛ አመት የኢኮኖሚክስ ተማሪ ቸሬ ሙላው በበኩሉ ''ተምሮ ሀገርና ህዝብን ማገልገል ራእይ ስላለኝ ትምህርቴን በአግባቡ እከታተላለሁ'' ሲል ተናግሯል፡፡ ''ሰላማዊ የመማር ማስተማር ስራን ማጠናከር ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች ቀዳሚ አጀንዳ ነው'' ያለው ተማሪ ቸሬ ''በኢትዮጵያዊነት መንፈስ ከአቻ ወንድሞቼ ጋር ትምህርቴን በአግባቡ ለመከታተል ወደ ዩኒቨርሲቲው በሰላም መጥቻለሁ'' ብሏል፡፡ የዩኒቨርሲቲው የተማሪዎች ህብረት አመራር አባል የሆነው ይበልጣል አበበ በበኩሉ ህብረቱ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲሳለጥ እገዛ ለማድረግ የተቋቋመ በመሆኑ ካለፈው አመት ጀምሮ ይህን ተልእኮውን እየተወጣ ነው ብሏል፡፡ ዩኒቨርሲቲ ማለት ትንሿ ኢትዮጵያ እንደመሆኑዋ ተማሪዎች የመጀመሪያ ተልእኮአቸው ትምህርት መሆኑን ተገንዝበው ወላጆችና ሀገሪቱ የጣለችባቸውን የዜግነት ሃላፊነት እንዲወጡ ህብረቱ ሃላፊነቱን እንደሚወጣ አስታውቋል፡፡ የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክና ምርምር ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር አበጀ ታፈረ ዩኒቨርሲቲው በዘንድሮ የትምህርት ዘመን አንድ ሺህ የሚጠጉ ነባር ተማሪዎችን ለማስተናገድ ተገቢውን ቅድመ ዝግጅት ማድረጉን ተናግረዋል፡፡ በተለይም ባለፈው አመት በመማር ማስተማር ስራው ላይ እንደ ችግር የተስተዋሉ የመብራት መቆራረጥና የቤተ-መጻህፍት የግብአት አቅርቦት ችግር ለመቅረፍ የጄኔሬተር ግዢና የዲጂታል ላይበራሪ የማቋቋም ስራ መከናወኑን ገልጸዋል፡፡ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ስራ ተጠናክሮ እንዲቀጥልም ከተማሪዎች ህብረት ጋር በመቀናጀት ተማሪዎች በእውቀትና በክህሎት ብቁ ሆነው እንዲወጡ ዩኒቨርሲቲው ተገቢውን ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ባለፈው አመት በይፋ ስራውን የጀመረው የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ በዘንድሮ የትምህርት ዘመን በ20 የትምህርት መስኮች በመጀመሪያ ዲግሪ መርሃ ግብር 2ሺ 600 አዲስና ነባር ተማሪዎችን እንደሚያስተናግድ ከዩኒቨርሲቲው የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም