ዩኒየኑ በተፈጥሮአዊ መንገድ የተመረተ ሰሊጥን ለውጪ ገበያ ለማቅረብ እየሰራ ነው

58
ጎንደር ጥቅምት 27/2011 በጎንደር ከተማ የሚገኘው ጸሃይ የገበሬዎች ህብረት ስራ ዩንየን በተፈጥሮአዊ መንገድ የተመረተ ሰሊጥን ለውጪ ገበያ በማቅረብ ከ3 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጪ ምንዛሬ ለማስገኘት አቅዶ እየሰራ መሆኑን አስታወቀ፡፡ በ2009/10 ምርት ዘመን በማእከላዊ ጎንደር ዞን 3 ወረዳዎች የሚገኙ ከ20ሺ በላይ አርሶ አደሮች ሰሊጥን ከተባይና ከአረም መከላከያ ኬሚካል እንዲሁም ከሰው ሰራሽ ማዳበሪያ ነጻ በሆነ መንገድ አልምተዋል፡፡ የዩንየኑ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ እንዳልካቸው አቤ ለኢዜአ እንደተናገሩት ዩንየኑ በዘንድሮ አመት በተፈጥሮአዊ መንገድ የለማ 30ሺ ኩንታል ሰሊጥ ለውጪ ገበያ ለማቅረብ አቅዶ እየሰራ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅትም በዞኑ 3 ወረዳዎች የሰሊጥ ግዢ ጣቢያዎችን ከማቋቋም ጀምሮ የሰሊጥ ማከማቻ መጋዘኖችን የማደራጀት እንዲሁም የግዢ ባለሙያዎችን የመመደብ ስራ እያከናወነ ነው፡፡ ዩንየኑ ከአርሶ አደሩ የሚረከበውን ሰሊጥ ከወቅቱ የገበያ ዋጋ በኩንታል ከ100 እስከ 150 ብር ጭማሪ አድርጎ በመረከብ አምራቹን ተጠቃሚ ለማድረግ ማቀዱንም ተናግረዋል፡፡ ''ከአረምና ተባይ መከላከለያ ኬሚካሎች እንዲሁም ከሰው ሰራሽ ማዳበሪያ ነጻ በሆነ መንገድ የሚመረተው ሰሊጥ ለአውሮፖ ገበያ  የሚቀርብ ነው'' ብለዋል፡፡ በዚህም ዩንየኑ አርሶ አደሩን የምርቱ ተጠቃሚ ከማድረግ በዘለለ ከ3 ሚሊዮን ዶላር በላይ ለሀገሪቱ የውጪ ምንዛሬ ለማስገኘት አቅዶ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ባለፈው አመት ዩንየኑ በተመሳሳይ መንገድ ለአውሮፓ ገበያ ከላከው 27ሺ ኩንታል ሰሊጥ ከ3 ሚሊዮን ዶላር በላይ የውጪ ምንዛሬ አስገኝቷል፡፡ የተፈጥሮ ማዳበሪያን በመጠቀምና ከማናቸውም ኬሚካል ነጻ የሆነ ሰሊጥ በ4 ሄክታር መሬት ላይ እያለማ መሆኑን የተናገረው የምስራቅ በለሳ ወረዳ ነዋሪ ወጣት አርሶ አደር አዲሱ ጌጡ ነው፡፡ ባለፈው አመት በተፈጥሮአዊ መንገድ ያመረተው ሰሊጥ ተቀባይነት በማግኘቱ ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት መቀበሉን የሚናገረው አርሶ አደር አዲሱ በዘንድሮ ምርት ዘመን የሚያገኘውን ሰሊጥ ለዩንየኑ ለማስረከብ መዘጋጀቱን ተናግረዋል፡፡ በተፈጥሮአዊ መንገድ የሚመረት ሰሊጥ በአለም ገበያ በዋጋ ደረጃ ተፈላጊነቱ እየጨመረ መጥቷል የሚለው ደግሞ በወረዳው የጣሊ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ሙቀት ንጉሴ ናቸው፡፡ በተፈጥሮአዊ መንገድ አርሶ አደሩ ያመረተውን ሰሊጥ ዩንየኑ ከገበያ ዋጋ በኩንታል ከ100 እስከ 150 ብር ጭማሪ በማድረግ እንደሚረከባቸው ውል ገብቶልናል ብለዋል፡፡ የምስራቅ በለሳ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ መልካሙ ሙሃባው በወረዳው 21 ቀበሌዎች 10ሺ የሚጠጉ አርሶ አደሮች በተፈጥሮ ሰሊጥ ልማት መሰማራታቸውን ገልጸዋል፡፡ ምርቱን ተቀባይ ከሆኑት የአውሮፓ ሀገራት የተፈጥሮ ሰሊጥ አምራችነት ማረጋገጫ የምስክር ወረቀት የወረዳው አርሶ አደሮች ባለፈው አመት አግኝተዋል ያሉት ሃላፊው ምርቱም በዩንየኑ በኩል ወደ ሀገራቱ እንደሚላክ ተናግረዋል፡፡ በ2010/11 ምርት ዘመን በማእከላዊ ጎንደር ዞን  ከ40ሺ ሄክታር በላይ የእርሻ መሬት በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ መንገድ ሰሊጥ መልማቱን የተናገሩት ደግሞ የዞኑ ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ግዛቸው ጀመረ ናቸው፡፡ በዞኑ በምእራብና ምስራቅ በለሳ እንዲሁም በኪንፋዝ በገላ ወረዳዎች 20ሺ አርሶ አደሮች በ6ሺ ሄክታር የእርሻ መሬት ላይ ሰሊጥን በተፈጥሮአዊ መንገድ አልምተዋል፡፡ በዞኑ በ2010/11 ምርት ዘመን በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ መንገድ ከለማው ሰሊጥ 320 ሺ ኩንታል ምርት እንደሚገኝ  በቅርቡ የተካሄደው የመስክ ግምገማ እንደሚያመላክት ኃላፊው አስታውቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም