በምዕራብ ጎንደር ዞን ሰሞኑን ተፈጥሮ የነበረውን አለመረጋጋት ወደ ሰላማዊ ሁኔታ ለመመለስ እየተሰራ ነው

83
ባህር ዳር  ጥቅምት 26/2011 በምዕራብ ጎንደር ዞን ሰሞኑን ተፈጥሮ የነበረውን አለመረጋጋት ወደ ሰላማዊ ሁኔታ ለመመለስ እየተሰራ መሆኑን የዞኑ ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ። የመምሪያው ኃላፊ ኮማንደር ጌትነት አልታሰብ ለኢዜአ እንደገለጹት ካለፈው ሳምንት ጀምሮ የህብረተሰቡን ሰላማዊ የእለት ተዕለት እንቅስቃሴ የሚገታ አለመረጋጋት በዞኑ ተከስቶ ነበር። በአካባቢው ማንነታቸው ባልታወቀና በተደራጁ ኃይሎች ተደጋጋሚ መኪና አቁሞ የመዝረፍ ድርጊት ሲፈፀም መቆየቱን ያስታወሱት ኮማንደሩ በመንግስት ተቋማት ተቀጥረው የሚሰሩ የቅማንት ተወላጆች ሥራቸውን ለቀው እንዲወጡ ሲደረግ መቆየቱንም ገልጸዋል። በትናንትናው ዕለትም የአዳኝ አገር ጫቆ ወረዳ መመስረትን ተከትሎ በወረዳው በምትገኝና ነጋዴ ባህር በተባለች አነስተኛ ከተማ የተዘጋጀውን በዓል አክብረው ወደ ቤታቸው ሲመለሱ በነበሩ ሰዎች ላይ በተከፈተ ተኩስ ጉዳት ከመድረሱ ጋር ተያይዞ በአካባቢው የባሰ አለመረጋጋት መፈጠሩን ገልፀዋል። የቅማንትንና የአማራን አብሮ ያደገ፣ የተዋለደና የተዋሀደ ህዝብ በማንነታቸው ግጭት ለመፍጠር የሚጥሩ አካላት ችግሩን አድርሰውታል የሚል ግምት እንዳለም ኮማንደር ጌትነት ጠቁመዋል። በተከሰተው ችግርም የሰው ሕይወት ከማለፉ በተጨማሪ የመቁሰል አደጋም መከሰቱን ነው የገለጹት። እንደ ኮማንደር ጌትነት ገለጻ ተፈጥሮ በነበረው አለመረጋጋት የትራንስፖርት አገልግሎትን ጨምሮ ሌሎች የህብረተሰቡ የእለት ከዕለት እንቅስቃሴዎች ተገድበው ቆይቷል። በአሁኑ ወቅት ህብረተሰቡንና የአካባበውን ወጣት በማነጋገር አካባቢው ወደ ቀደመ ሰላማዊ ሁኔታ እንዲመለስ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል። ወደተለያዩ ከተሞች የሚሄዱ ተሽከርካሪዎች በፀጥታ ኃይል ታጅበው እንዲንቀሳቀሱ እየተደረገ ሲሆን በአካባቢው ላይ የፀጥታ አካላት ቅኝት እንዲያደርጉ መመደባቸውንም ኮማንደር ጌትነት አብራርተዋል። የአካባቢው ሰላም ሙሉ ለሙሉ እንዲመለስም የኢፌድሪ መከላከያ ሠራዊት አበላትና ሌሎች የፀጥታ አካላት በጋራ እየሰሩ መሆኑን ጠቁመው፣ "ወንጀል የፈፀሙ አካላትን በቁጥጥር ስር ለማዋልም ጥረት እየተደረገ ነው" ብለዋል። ሰላምን ማስከበር የፀጥታ አካሉ ሥራ ብቻ ሳይሆን ሕብረተሰቡም የፀጥታ ችግር የሚፈጥሮ አካላትን በማጋለጥ ከፀጥታ አካሉ ጋር ተባብሮ ሊሰራ እንደሚገባ አስግንዝበዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም