እምቦጭን በዘላቂነት ለመከላከል ጥረት እየተደረገ ነው—አቶ ገዱ አንዳርጋቸው

2132

ባሀርዳር ጥቅምት 26/2011 የጣና ሀይቅን ከእምቦጭ አረም በዘላቂነት ለመከላከል የማስወገጃ ማሽኖችና የአርሶ አደርሩን ጉልበት በመጠቀም ጥረት እየተደረገ መሆኑን የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ገለጹ፡፡

የባህር ዳር ዩኒቨርስቲ ያሰራቸው  አራት የእምቦጭ ማስወገጃ  ማሽኖች ተመርቀው  የሙከራ ስራ ጀመረዋል፡፡

በዚህ ወቅት ርዕሰ መስተዳደሩ እንዳሉት  አርሶ አደሮችና ሌሎችም የሃይቁ ተጠቃሚ አካላት በጣና ላይ የተደቀነውን አደጋ ለመቀነስ ተቀናጅቶና ተናቦ መስራት የግድ ነው፡፡

“አረሙን በዘላቂነት ለመከላከል አዳዲስ ማሽኖችን፣ የአርሶ አደርሩን ጉልበትና በስነ ህይዎታዊ ዘዴ አቀናጅቶ በመጠቀም ለመከላከል ጥረት እየተደረገ ነው” ብለዋል፡፡

“በተለይም የክልሉ መንግስት የአርሶ አደሩን ጉልበት በዋናነት በመጠቀም ሌሎችን ሳይጠብቅ እምቦጭን ብቻ ሳይሆን ሃይቁ ከተደቀኑበት ሌሎች አደጋዎች በመጠበቅ  ኃላፊነታችን ለመወጣት የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን “ብለዋል።

የባህር ዳር ዩኒቨርስቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ፍሬው ተገኝ በበኩላቸው ከሙላት ኢንዱስትሪያል ኢንጅነሪንግ ሃላፊነቱ ከተወሰነ የግል ማህበር ጋር በመተባበር ከ19 ሚሊዮን ብር በሚበልጥ ወጪ ያሰሯቸው አራቱ ማሽኖች የሙከራ ስራ ማስጀመራቸውን አስታውቀዋል፡፡

አረሙን በስነ ህይዎታዊ ዘዴ ለማስወገድም  ጢንዝዛዎችን ከውጭ በማስማጣት የማባዛት ስራ እያከናወነ መሆኑን ጠቁመው “በሃይቁ ዙሪያ የደንገል ተክልን በማስፋፋት እንቦጭን ለመከላከል የሚያስችሉ ፕሮጀክቶችን ነድፈን እየሰራ ነው “ብለዋል።

“የእምቦጭ አረሙን በመከላከል የአርሶ አደሩ ጉልበት ሙሉ በሙሉ የሚተካ አማራጭ የለም ” ያሉት ደግሞ የአማራ ክልል ደን፣ ዱር እንስሳትና አካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር በላይነህ አየለ ናቸው።

አርሶ አደሩን የሚያግዙ አዳዲስ ማሽኖችን ለማስገባት ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ ገልጸው እንቦጩን ከማስወገድ በተጨማሪ ወደ ሃይቁ የሚገባውን ደለልና ፍሳሽ ቆሻሻ መከላከል እንደሚገባም ጠቁመዋል።

በማዕከላዊ ጎንደር ዞን የሸሃ ጎመንጌ አካባቢ ነዋሪዎች መካከል አርሶ አደር ሙላቴ አሰፋ በሰጡት አስተያየት የእምቦጭ አረም ከተከሰተ ጊዜ አንስቶ በጉልበታቸው ለመከላከል  ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸውን ተናግረዋል።

በዚሀም አረሙን መከላከልና የስርጭት መጠኑን መቀነስ ተችሎ እንደነበር አስታውሰዋል።

ሆኖም  ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ የእምቦጭ የስርጭት መጠን እየተስፋፋ ከአርሶ አደሩ አቅም በላይ በመሆኑ አካባቢውን እየወረረው መምጣቱ አመልክተዋል።

አርሶ አደሩ እንዳሉት የእምቦጭ አረሙ ሃይቁን በመውረሩ የተነሳም አሳ ማስገር፣ ታንኳም ሆነ ጀልባ ይዞ መንቀሳቀስ አልተቻለም፤ በሃይቁ ዙሪያ የሚገኘውን አርሶ አደር ለጉዳት ተጋልጧል፤  መንግስት ዘላቂ መፍትሄ ሊያበጅ ይገባል፡፡

አርሶ አደር አምባው መንግስቴ በበኩላቸው የእንቦጭ አረሙን በልማት ቡድን በመደራጀት ጭምር ለሰባት ዓመታት ሲያርሙ መቆየታቸውን ገልጸዋል፡፡

አርሶ አደሩ እንቦጭን ለማረም ከመደበኛ የእርሻ ስራው እየወጣ በመምጣቱ መንግስት ተገቢውን በጀት በመመደብ ወጣቱን በማሰማራት በዘላቂነት የማስወገድ ስራ ሊያከናውን እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡