በኢትዮጵያ አስተማማኝ ሰላም ለማምጣት አገር በቀል የግጭት አፈታት እሴቶችን ማጎልበት ያስፈልጋል-ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ

183
አዲስ አበባ   ጥቅምት  26/2011 በኢትዮጵያ አስተማማኝ ሰላም ለማምጣት አገር በቀል የሆኑ የግጭት አፈታት እሴቶችን ማጎልበት እንደሚገባ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ተናገሩ። እርቅ ላይ የሚሰሩ ሴቶችን ማፍራት እንደሚያስፈልግም ጠቁመዋል። አገር አቀፍ የኢትዮጵያ ሴቶች የሰላም ኮንፈረንስ ''ሴቶች ዘረኝነትን በመጠየፍ ለሰላማችን ግንባር ቀደም ሚናችንን እንወጣ'' በሚል መሪ ቃል ዛሬ በአዲስ አበባ ተካሂዷል። በዚህ ወቅት ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ እንዳሉት፤ በአገሪቱ አስተማማኝ ሰላም ለማምጣት ሴቶች ባካበቱት አገር በቀል የግጭት አፈታት ተግባር ሊበረታቱ ይገባል። በከፍተኛ የስራ የሃላፊነት ቦታ ያሉ ሴቶች አስታራቂ፣ ቀናና ብሩህ አእምሮ ያላቸውን ሴቶች በማፍራት ረገድ ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ ይገባል ብለዋል። የሰላም እጦት በሚያስከትለው መዘዝ ግምባር ቀደም ገፈት ቀማሾች ሴቶችና ህጻናት በመሆናቸው ሴቶች ከመቼውም ጊዜ በላይ ለሰላማቸው ዘብ መቆም እንዳለባቸው ፕሬዚዳንቷ አስገንዝበዋል። ሴቶች በመንግስት ከተሰጣቸው ሃላፊነት በተጨማሪ በአገራቸውና በቤተሰቦቻቸው የሚታዩ የሰላም እጦቶች የመፍትሄ አካል መሆናቸውን  መቀጠል አለባቸው ብለዋል። በተጨማሪ መንግስት በሴቶች ላይ ያለውን አመኔታ በተግባር በመለወጥ ለብዙ ተከታዮቻቻው አረአያ መሆን ይጠበቅባቸዋል። ሴቶች ወደ አመራርነት እንዲመጡ መስዋዕትነትን ለከፈሉ ምስጋና በማቅረብ ንግግራቸውን የጀመሩት የሰላም ሚኒስትር ወይዘሮ ሙፈሪሃት ካሚል በአገሪቱ አስተማማኝ ሰላም እንዲሰፍን ሴቶች ባላቸው ልምድና ተሞክሮ  ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮችን እንዲመክቱ ጠይቀዋል። በቅርቡ የተቋቋመው የሰላም ሚኒስቴር የታለመለትን አላማ እውን እንዲያደግ ሁሉም የበኩልን እንዲወጣ ጠይቀዋል። በአገር አቀፍ ኮንፈረንሱ ላይ ሚኒስትሮች፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ የክልል ከፍተኛ የስራ ሃላፊዎች፣ የፌዴራልና የክልል ምክር ቤት አባላት፣ አርቲስቶችና ታዋቂ ግለሰቦች እንዲሁም የተለያዩ የዓለም ዓቀፍ አካላት ተወካዮች ተገኝተዋል። የሰላም ኮንፈረንሱ ዋና አላማ በአገሪቱን ዘላቂ ሰላም ለማስፈን መንግስት እያከናወነ ያለውን ጥረት ለማገዝና ሴቶች የበኩላቸውን እንዲወጡ ለማድረግ ነው። በቀጣይም በሁሉም ክልሎች ተመሳሳይ መድረኮች እንደሚዘጋጁ ታውቋል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም