የአፍሪካ ቀን ከነገ በስቲያ ይከበራል

105
አዲስ አበባ ግንቦት 15/2010 የአፍሪካ ቀን ከነገ በስቲያ በአዲስ አበባ የአፍሪካ ህብረት መሰብሰቢያ አዳራሽ ይከበራል። "የአፍሪካ ህብረት አጀንዳ 2063" ዘንድሮ ለ55ኛ ጊዜ የሚከበረው የአፍሪካ ቀን መሪ ቃል ነው። ቀኑ የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (የአሁኑ የአፍሪካ ህብረት) እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ1963 መመስረትን አስመልክቶ የሚከበር ነው። ዕለቱ ሲከበር አህጉሪቱ እስካሁን በተለያዩ መስኮች ያስመዘገበቻቸውን ስኬቶች መዘከርና ቀጣይ ፈተናዎችን በምን አይነት መልኩ ማለፍ እንደሚቻል የሀሳብ ልውውጥ ይደረጋል። ቀኑ በታሪክና በባህል ሀብታም ናት የምትባለው አፍሪካ የአህጉሪቱ ህዝቦች እርስ በእርስ የባህል፣ የኪነ ጥበብና ሌሎች ልምዳቸውን የሚያስተዋውቁበት መድረክ ተደርጎም ይወሰዳል። የአፍሪካ አገራትና በተለያዩ የዓለም ክፍሎች የሚገኙ አፍሪካዊ ዳያስፖራዎችም ቀኑን ያከብሩታል። አጀንዳ 2063 የአፍሪካ ልማት ህዝቦቹ ላይ መሰረት ያደረገ፣ የአፍሪካን ህዝብ አቅም መጠቀም ላይ ያተኮረና ለሴቶች፣ ለወጣቶችና ህጻናት ቅድሚያ በመስጠት "የምንፈልጋትን አፍሪካ" ለማግኘት መስራት የሚለውን ግብ በዋነኛነት አንግቧል። በአፍሪካ ሀብረት ዋና መቀመጫ አዲስ አበባ በሚከበረው የአፍሪካ ቀን "አጀንዳ 2063"ን እውን ለማድረግ አገራት ማድረግ ስለሚገባቸው ጉዳይና የአፍሪካ ማንነትና አንድነት ላይ የፓናል ውይይት ይደረጋል ተብሎ ይጠበቃል። ከውይይቱ በተጨማሪም የአፍሪካን ባህልና ታሪክ የሚያሳዩ ትርኢቶች እንደሚቀርቡም ተገልጿል። የአፍሪካና ዓለም አቀፍ ተቋማት፣ ተማሪዎች፣ የሌሎች አገራት ዜጎችና አጋር አካላት የአፍሪካ ቀንን ያከብራሉ። ያለፈው ዓመት የአፍሪካ ቀን "በወጣቶች ላይ ኢንቨስት በማድረግ የህዝብን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ" በሚል መሪ ቃል መከበሩ ይታወሳል። ጋና፣ ዚምባብዌ፣ ሌሰቶ፣ ዛምቢያና ማሊ የአፍሪካ ቀን ብሔራዊ ክብረ በዓል እንዲሆን በማድረግ ቀኑን በደማቅ ሁኔታ ያከብሩታል። በዓሉ የአፍሪካ ቀን ከመባሉ በፊት የአፍሪካ የነጻነት ቀን እየተባለ ይከበር ነበር።    
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም