በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የደረሰ ሰብል በዝናብ እንዳይጎዳ የመሰብሰብ ሥራ ተጀምሯል

56
ፍቼ ጥቅምት 26/2011 በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በመኸር እርሻ በዘር ከተሸፈነው 475 ሺህ ሄክታር የደረሰ ሰብል ውስጥ ከፊሉ ወቅቱን ባለጠበቀ ዝናብ እንዳይጎዳ መሰብሰቡን የዞኑ ግብርና ጽህፈት ቤት አስታወቀ። የጽህፈት ቤቱ የሰብልና ኤክስቴንሽን ሥራ ሂደት ባለቤት አቶ ዱጉማ ሁንዴ ዛሬ እንደገለጹት አርሶ አደሮች የለፉበት ምርታቸው ባልጠበቁት ዝናብ ሳይባክን በአግባቡ እንዲሰበስቡ በባለሙያና በአስተዳደር አካላት ድጋፍ ተደርጎላቸዋል። በተለይ በአካባቢው ወቅቱን ያልጠበቀ ዝንብ በደረሰና በደረቁ የጤፍ፣ የስንዴ፣ የገብስና ሌሎች ሰብሎች ላይ ጉዳት ከማስከተሉ በፊት አርሶ አደሩ በቂ ዝግጅት በማድረግ እንዲከላከል ታቅዶ እየተሰራ መሆኑንም ገልፀዋል ። በአሁኑ ወቅት በዞኑ 13 ወረዳዎች በመኸር እርሻ በዘር ከተሸፈነው 475 ሺህ 455 ሄክታር መሬት ከ49 በመቶ በላይ የሚሆነው የደረሰ ስብል ተሰብስቦ በመወቃት ሂደት ላይ መሆኑን ተናግረዋል። በዞኑ ከሰብል ልማቱ 12 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለማግኘት ታቅዶ የተሰራ መሆኑን የገለጹት አቶ ዳጉማ፣ ምርቱ ሲሰበሰብ ብክነት እንዳይደርስበት ተገቢ ጥንቃቄ የተሞላበት አሰራር እንዲኖር አርሶ አደሮችን ከማሰልጠን ጀምሮ ስራዎች መሰራታቸውን ገልጸዋል። የተሰበሰቡ ሰብሎችም ሳይባክኑ በአርሶ አደሮች፣ በተማሪዎች፣ በመንግስት ሠራተኞችና በበጎ ፍቃደኛ ሰዎች ተወቅተው ጎተራ እንዲገቡ ጥረት በመደረግ ላይ መሆኑን አመልክተዋል። እንደ አቶ ዳጉማ ገለጻ ይህን ተግባር የሚያስተባብሩ የዞንና የወረዳ አካላት በየገጠሩ አካባቢ ተሰማርተው ተግባራዊ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ናቸው። የዞኑ የአዝርዕት ልማት በለሙያ አቶ ስመኝ ደበሌ የክረምቱ ዝናብ ስርጭት መስተካከል በአሁኑ ወቅት በአካባቢው ለተገኘው የተሻለ ምርት ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ገልጸዋል። በአሁኑ ወቅት አየጣለ ያለው ዝናብም በአንዳንድ የዞኑ አካባቢዎች ተፈላጊ መሆኑን አቶ ስመኝ ተናግረዋል። አርሶ አደሩ ወቅቱን ጠብቆ አረምን ማስወገዱ ብቻ ሳይሆን እየጣለ ያለውን ዝናብ ጉዳት ሳያስከትል ምርቱን በወቅቱ መሰብሰቡ ለምርት አድገትና ጥራት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያለው መሆኑን ተናግረዋል ። የደረሰ ሰብላቸውን በዘመቻ  በወቅቱ እንደሰበሰቡ የተናገሩት የወረጃርሶ ወረዳ የሴፈን ቀበሌ አርሶ አደር ግርማ ደበሌ፣ምርቱ መሰብሰቡ ዝናብ ያደርስባቸው የነበረውን የምርት ጉዳት ለመከላከል አንዳስቻላቸው ተናግረዋል። የተሰበሰበውን የጤፍ ሰብል ከጎረቤቶቻቸው ጋር በጋራ ለመውቃት እየተዘጋጁ መሆናቸውንም አርሶ አደሩ ተናግረዋል። "ሰብልን በወቅቱ ባይሆንም በዝናብ ጉዳት እንዳይደርስበት አስቀድሞ መሰብሰቡ ከስጋትና ብልሽት ያደናል" ያሉት በእዚሁ ወረዳ የጎልጄ ቀበሌ አርሶ አደር ደንደና መግርሳ ናቸው። "ምርት ቀድም ብሎ መሰብሰቡ ወደሌሎች የልማት ሥራ ለመሰማራት የተሻለ እድል ከመፍጠሩ ባሻገር በዝናብና በንፋስ ከሚከሰት የምርት በክነት እንደሚታደግ ከባለሙያ ምክር ግንዛቤ አግኝተናል" ብለዋል ። ሌሎች አርሶ አደሮችም ዝናብ ሊያስከትል የሚችለውን ጉዳት ለመከላከል በተናጠልም ሆነ በቡድን በመሆን ሰብላቸውን እንዲሰበስቡ መክረዋል። ።            
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም