በአብዛኛው የኢትዮጵያ ክፍሎች የሚኖረው ቅዝቃዜና ውርጭ በሰብል ላይ ጉዳት ሊያስከትል ስለሚችል ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል ተባለ

1604

አዲስ አበባ ጥቅምት 26/2011 በቀጣዮቹ 25 ቀናት በአብዛኛው የኢትዮጵያ ክፍሎች የሚኖረው ቅዝቃዜና ውርጭ በሰብሎች ላይ ጉዳት ሊያስከትል ስለሚችል ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ብሔራዊ የሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ አስታወቀ።

ኤጀንሲው ለኢዜአ  በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ በተጠቀሰው ጊዜ በአብዛኛው የኢትዮጵያ ክፍሎች ላይ የበጋው ደረቃማ የእርጥበት ሁኔታ የሚያመዝን እንደሆነና በአብዛኛው የመኸር ሰብሎች ስብሰባና የድህረ ሰብል የሚከናወንበት እንደሆነ ገልጿል።

በአንጻሩ የደቡብና ደቡብ አጋማሽ የአገሪቱ አካባቢዎች መጠነኛ የሆነ እርጥበት የሚያገኙበት ወቅት እንደሆነም ተመልክቷል።

በኤጀንሲው የአየር ትንበያ መሰረት በአብዛኛው የአገሪቱ ክፍሎች የበጋው ደረቃማ የእርጥበት ሁኔታ እንደሚያመዝን ይጠበቃል።

ከዚሁ ጋር ተያይዞ በአንዳንድ ደጋማ አካባቢዎች ላይ የሌሊቱና የማለዳው ቅዝቃዜ እንደሚጠናከርና የውርጭ ክስተት ሊኖር እንደሚችልም ተጠቅሷል።

ደረቃማው የእርጥበት ሁኔታ የሰብል ስብሰባና የድህረ ሰብል ስብሰባን በስፋት ለማከናወን መልካም አጋጣሚ እንዳለውም ኤጀንሲው አስታውቋል።

ያም ቢሆን ከጠንካራ ቅዝቃዜና ከውርጭ ክስተት ጋር ተያይዞ አንዳንድ እድገታቸውን ያልጨረሱና በተለይም በአበባና በዘር ሙሌት ላይ ለሚገኙ ሰብሎችና የፍራፍሬ ተክሎች ላይ ጉዳት ሊያስከትል ስለሚችል አርሶ አደሮች ከሚመለከታቸው አካላት አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ኤጀንሲው አሳስቧል።

በሌላ መልኩ በአንዳንድ የምዕራብ፣ የደቡብ፣ የደቡብ ምስራቅና የምስራቅ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ከመደበኛ ጋር የተቀራረበ እርጥበት እንደሚኖራቸው በትንበያው ተጠቅሷል።

ይህም ሁኔታ በእድገት ላይ ለሚገኙ የበጋ ወቅት ሰብሎች ለግጦሽ ሳርና ለመጠጥ ውሃ አቅርቦት በጎ ጎን ቢኖረውም የደረሱና ያልተሰበሰቡ ሰብሎችን ሊጎዳ ስለሚችል አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አመልክቷል።

በቀጣዮቹ 25 ቀናት የገናሌ ዳዋ የዋቢ ሸበሌ፣ መካከለኛውና የታችኛው አባይና የስምጥ ሸለቆ፣ ደቡባዊው የአባይ ክፍል እንዲሁም ጥቂት የላይኛው የባሮ አከቦ ተፋሰሶች ከመደበኛው ጋር የተቀራረበ የዝናብ መጠን እንደሚያገኙ የኤጀንሲው ትንበያ ያሳያል።

ዝናብ ሚያገኙ ተፋሰሶች ላይ የሚገኘው ማህበረሰብና በውሃ እንቅስቃሴ ላይ የሚሰሩ ተጠቃሚዎች በታቸለ መጠን የሚገኘውን ውሃ በአግባቡ በመያዝ ለሚያስፈልገው እንቅስቃሴ እንዲያውሉ ኤጀንሲው ገልጿል።

በቀጣዮቹ 25 ቀናት ደረቃማ የአየር ጠባይ በአብዛኞቹ የኢትዮጵያ ክፍሎች ላይ ተጠናክሮ እንደሚቆይና ከዚሁ ጋር በተያያዘም በአንዳንድ የአገሪቱ ስፍራዎች የሌሊቱና የማለዳው ቅዝቃዜ ሊጨምር እንደሚችል ትንበያው ያመለክታል።

ከዚህም ሌላ አልፎ አልፎ ከሚጠናከሩ የደመና ክምችቶች ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚኖር ከኤጀንሲው የተገኘው መረጃ ያሳያል።