በአፍሪካ ግጭቶች ከተከሰቱ በኋላ ዘላቂነት ያለው የመልሶ ማቋቋም ስራዎች ክፍተት ዋና ተግዳሮት መሆኑ ተገለጸ

89
አዲስ አበባ ጥቅምት 26/2011 በአፍሪካ ግጭቶች ከተከሰቱ በኋላ ዘላቂነት ያለው የመልሶ ማቋቋም ስራዎች ክፍተት ዋና ተግዳሮት መሆኑን የኢትዮጵያ የሰላም ማስከበር ማዕከል አስታወቀ። ማዕከሉ ከጃፓን መንግስትና 'ዩ ኤን ዲፒ' ጋር በመሆን ከግጭት በኋላ መልሶ ማገገም ላይ ያተኮረ ለሁለት ሳምንት የሚቆይ ስልጠና ዛሬ ተጀምሯል። በስልጠናው መክፈቻ ላይ የማዕከሉ የሰላም ማስከበር ዋና መምሪያ ተጠባባቂ  አዛዥ ብርጋዴር ጄነራል ሀብታሙ ጥላሁን እንደገለጹት በአፍሪካ ቀንድ ከሚከሰቱ ግጭቶች በኋላ ዘላቂነት ያለውና ተጨባጭ የሆኑ የመልሶ መገንባትና ልማት ስራዎች እጦት አንዱ ችግር ነው። ፖለቲካዊ ግጭቶች፣ የልማት እጦትና ኋላ ቀርነት ደግሞ ግጭቶቹ በተደጋጋሚ እንዲከሰቱ መንስኤ መሆኑን ነው የገለጹት። በመሆኑም ከግጭቶች በኋላ የመልሶ መገንባትና የልማት ስራዎች ላይ ትኩረት በመስጠት መስራት አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል። የበለጸገችና ሰላማዊ አፍሪካን በመፍጠር በዓለም አቀፍ ደረጃ ተጽዕኖ ፈጣሪ ለመሆን እራሳቸው አፍሪካውያን ንቁ ተሳትፎ ሊኖራቸው እንደሚገባም አክለዋል። ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታትና የአፍሪካ ሕብረት የሰላም ማስከበር ስራዎችን  ለመደገፍ ቁርጠኛ በመሆኗ የሰላም ማስከበር የስልጠና ማዕከል መቋቋሙንም አንስተዋል። ማዕከሉ በዓለም አቀፍ ደረጃም ተመራጭ ለመሆን እየሰራ ነው ብለዋል። በማዕከሉ የሰላምና ደህንነት የትምህርት ክፍል የስልጠና ኃላፊ አቶ ዳዊት አሰፋ ከሰላም ማስከበርና ግጭት አፈታት ጋር የተያያዙ በየዓመቱ ወደ 25 የሚሆኑ ስልጠናዎች እንደሚሰጡ ገልጸዋል። በስልጠናው ከዘጠኝ የአፍሪካ አገራት የተውጣጡ  በሰላም ማስከበር ስራዎች ላይ የሚሰሩ 29 ባለሙያዎች(ኤክስፐርቶች) ተካተዋል ብለዋል። የስልጠናው ተሳታፊዎች ከፖሊስ፣ ከመከላከያ ኃይልና ከሲቪሉ የሕብረተሰብ ክፍል የተውጣጡ መሆናቸውንም አክለዋል። ስልጠናው  ግጭቶች ውስጥ የነበሩ አገራት የሚያጋጥሟቸው ችግሮች መውሰድ ስለሚኖርባቸው የመፍትሄ እርምጃዎችና ዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች ላይ ያተኮረ መሆኑንም አብራርተዋል። በሰላም ግንባታ፣ መልሶ ማቋቋምና የልማት ስራዎች ላይም አስፈላጊውን ዕውቀትና ክህሎት የሚያስጨብጥ ነው ያሉት። በኢትዮጵያ የጃፓን አምባሳደር ሚስተር ዳይሱኪ ማትሱናጋ በበኩላቸው ኢትዮጵያ በአፍሪካ የሰላም ማስከበርና ደህንነት ማስጠበቅ ላይ ለምታደርገው ያላሰለሰ ጥረት ያላቸውን አድናቆት ገልጸዋል። ከግጭቶች በኋላ የመልሶ ማቋቋም ስራዎችን ማጠናከር ግጭቶች ተመልሰው እንዳይፈጠሩ ለማድረግ ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው ስልጠናው በዚህ ረገድ አስፈላጊውን ክህሎትና ዕውቀት ለማስጨበጥ እገዛ እንደሚኖረውም ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም