የአክሱም ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በተደረገላቸው ቤተሰባዊ አቀባበል መደሰታቸውን ገለጹ

84
አክሱም ጥቅምት 25/2011 በአክሱም ከተማ ነዋሪዎችና በዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ በተደረገላቸው ቤተሰባዊ አቀባበል መደሰታቸውን የአክሱም ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ገለጹ፡፡ ከተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ወደ ዩኒቨርሲቲው የተመደቡ ተማሪዎች በከተማው ነዋሪ ህዝብና በዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡ ከደቡብ ክልል ሲዳማ ዞን ወደ ዩኒቨርሲቲው የተመደበ ተማሪ አለማየው ቶማስ እንዳለው ማህበረሰቡ ያደረገላቸው አቀባበል በስነልቦና እንዲጠነክሩ ጠቀሜታው የጎላ ነው፡፡ በዩኒቨርሲቲ ቆይታው ውጤታማ ተማሪ ለመሆንና የመጣበትን ዓላማ ለማሳካት ጠንክሮ እንዲማር ተማሪ ቶማስ ተናግሯል፡፡ ከነገሌ ቦረና የመጣችው ተማሪ ሂወት ለገሰ በበኩሏ ተማሪው እንግልት እንዳይደርስበት በሁሉም አቅጣጫ ተሸከርካሪዎች በመመደብ የተደረገላቸው አቀባበል ቤተሰባዊ ስሜት እንዲሰማት ያደረጋት መሆኑን ገልጻለች፡፡ በዩኒቨርሲቲ ቆይታዋ  ከትምህርቷ በተጨማሪ በከተማው በሚከናወኑ የተለያዩ በጎ ፈቃድ አገልግሎቶችና ማህበራዊ ግንኙነቶች ላይ ለመሳተፍ ፍላጎት እንዳላት ተናግራለች። ህዝቡ ያደረገላቸው አቀባበል አሜነታ እንዳሳደረባቸው የተናገሩት ደግሞ  ከኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን አሰላ ከተማ ተማሪ ልጃቸውን ይዘው የመጡ አቶ ሙላት ገብረማርያም  ናቸው፡፡ ከልጃቸው ጋር ወደአክሱም ዩኒቨርሲቲ መምጣታቸው የአክሱም ታሪካዊ ሥፍራዎችን ለመጎብኘት እንዳስቻላቸውም ተናግረዋል፡፡ ተማሪ ልጃቸውን ከአዲስ አበባ ወደ ዩኒቨርሲቲው ይዘው የመጡ ወይዘሮ ትዕግስት ማሩፋ በበኩላቸው ከአዲስ አበባ ጀምሮ እስከ አክሱም ከተማ ድረስ ሰለማዊ ጉዞ እንደነበረ ገልጸዋል። "በወሬ የሚናፈሰውና በተግባር ያየነው  የተለያየ  ነው" ብለዋል፡፡ በመልእክታቸውም  "ማየት ማመን ነው፤ የህዝቡ ትብብርም በዚሁ ይቀጥል" ብለዋል፡፡ የዩኒቨርሲቲው አከዳሚ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር ኪሮስ ጉዕሽ በበኩላቸው ዘንድሮ የሚገቡ 5 ሺህ የሚጠጉ አዲስ ተማሪዎችን ለመቀበል ዝግጅት ሲያደርጉ መቆየታቸውን ተናግረዋል፡፡ ዓመቱም ሰለማዊ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲኖር ከአካባቢውና ከዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ አመልክተዋል፡፡ "ለተማሪዎቹ  የመብት ጥያቄ ተገቢ ምላሽ በወቅቱ በመስጠት የተሻለ የትምህርት እንቅስቃሴ እንዲኖር ዩኒቨርሲቲው አተኩሮ ይሰራል" ብለዋል። የትምህርት ጥራት ለማረጋገጥ  የሚያስችል በቂ የመሰረተ ልማትና የሰው ኃይል መሟላቱንም ጠቁመዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም