በ361 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ሥራው የተከናወነው የመቀሌ የንፁህ መጠጥ ውሃ ማስፋፊያ ግንባታ ተመረቀ

1831

መቀሌ ጥቅምት 25/2011 በመቀሌ ከተማ ግንባታው በ361 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የተካሄደው የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ማስፋፊያ ሥራ ተጠናቆ በክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል ዛሬ ተመረቀ።

በማስፋፊያ ግንባታው ከመቀሌ ከተማ በ30 ኪሎ ሜትር ርቀት በእንደርታ ወረዳ ልዩ ስሙ “ጭንፈረስ” በተባለ አካባቢ 10 ጥልቅ የውሃ ጉድጓዶች ለአገልግሎት ተዘጋጅተዋል።

የመቀሌ ከተማ መጠጥ ውሃ አገልግሎት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ጊደና አበበ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት ለማስፋፊያ ግንባታው የዋለው ገንዘብ ከክልሉ ውሃ ሀብት ቢሮ፣ ከከተማው አስተዳደርና፣ ከዓለም ባንክ የተገኘ ነው ።

የንፁህ መጠጥ ውሃ ማስፋፊያ ግንባታ ሥራው በገንዘብ፣ በቁሳቁስና በባለሙያ እጥረትና ሌሎች ምክንያቶች ከ10 ዓመት ጊዜ በላይ መፍጀቱን ተናግረዋል ።”ለአገልግሎት የተዘጋጁት ጥልቅ የውሃ ጉድጓዶች እያንዳንዳቸው በሰከንድ እስከ 50 ሊትር ውሃ የማመንጨት አቅም አላቸው ” ብለዋል ።

ጉድጓዶቹ ለከተማው ህዝብ  በቀን በአማካይ እስከ 21ሺህ ሜትር ኩብ ውሃ የማቅረብ አቅም ያላቸው መሆኑንም ኃላፊው ተናግረዋል ።

“በተቆፈሩት ጥልቅ የውሃ ጉድጓዶች የከተማው የንፁህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ሽፋን አሁን ካለበት 53 በመቶ ወደ 68 በመቶ ያድጋል” ያሉት ኃላፊው ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የከተማው ነዋሪዎች በቂ የውሃ አቅርቦት እንደሚያገኙ አመላክተዋል።

በከተማው ከሚቀርበው የንፁህ ውሃ ውስጥ በተለያዩ ምክንያቶች እየደረሰ ያለውን 25 በመቶ ብክነት ለመቀነስ ህብረተሰቡ አጠቃቀሙን በማስተካከል የድርሻውን እንዲወጣ ኃላፊው ጥሪ አቅርበዋል ።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል በወቅቱ እንደገለፁት የመቀሌ ከተማው የንፁህ መጠጥ ወሃ አቅርቦት እጥረትን በዘላቂነት ለመፍታት ከተቆፈሩት አስር ጥልቅ ጉድጓዶች በተጨማሪ ሌላ የማስፋፊያ ግንባታ እየተካሄደ ነው ።

ከከተማው በስተደቡብ አቅጣጫ የተጀመረው የ”ገረብ ሰገን‘‘ የውሃ ግድብ ግንባታ ሥራ በአሁኑ ወቅት እየተፋጠነ መሆኑን ለአብነት ጠቁመዋል ።

በተጨማሪም ከከተማው በስተምዕራብ  አቅጣጫ የ”ገረብ ግባ”  ግድብ ግንባታ ስራ በቅርቡ እንደሚጀመር አመላክተዋል።

በክልሉ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግርን ለመፍታት እየተደረገ  ባለው ጥረት በተለይም የፌዴራል መንግስት ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ዶክተር ደብረፅዮን ጠይቀዋል ።

የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጅነር ስለሺ በቀለ በበኩላቸው እንዳሉት በትግራይ የውሃ ሃብትን ጥቅም ላይ ለማዋል በመንግስትና በህዝቡ እየተደረገ ያለው የተቀናጀ ጥረት ለሌሎች ክልሎች አርአያ የሚሆን ነው ።

“ያለ ዘላቂ የውሃ ሃብት በአገሪቱ ዘላቂ የኢንቨስትመንት ልማት አይረጋገጥም” ያሉት ሚኒስትሩ በየክልሉ የሚገኙ አመራሮችና ባለሙያዎች የውሃ ሀብትን ጥቅም ላይ ለማዋል ተገቢ ትኩረት እንዲሰጡ አስገንዝበዋል ።

ከመቀሌ ከተማ ነዋሪዎች መካከል አቶ በርሄ አርከበ በበኩላቸው በሰጡት አስተያየት ቁፋሯቸው ተጠናቆ የተመረቁት ጥልቅ ጉድጓዶች የህዝቡን የውሃ እጥረት ይፈታልን ጥያቄ የመለሱ መሆናቸውን ተናግረዋል ።

ነዋሪው ለውሃ አጠቃቀም ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ ግንዛቤ በማስጨበጥ የበኩላቸውን እንደሚወጡም አቶ በርሄ አስታውቀዋል ።