አረጋዊያን ልምዳቸውን ለተተኪው ትውልድ እንዲያስተላልፉ ሊታገዙ ይገባል ተባለ

105
ባህር ዳር  ጥቅምት 25/2011 አረጋዊያን በዕድሜ ዘመናቸው ያካበቱትን ልምድና መልካም ተሞክሮ ለተተኪው ትውልድ እንዲያስተላልፉ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ከጎናቸው ሆኖ ሊያግዛቸው እንደሚገባ ተገለጸ። 28ኛው ዓለም አቀፍ የአረጋዊያን ቀን በአማራ ክልል ደረጃ በባህር ዳር ከተማ ሙሉአለም የባህል ማዕከል ዛሬ ተከብሯል። በዓሉ በፓናል ውይይት ሲከበር የቀድሞው የክልሉ ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሞላ ጀምበሬ እንደተናገሩት በአስቸጋሪ የኑሮ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ አረጋዊያንን ለመደገፍ እየተሰራ ነው። እስካሁን በተሰራው ስራ በባህር ዳር ለአረጋዊያን የገቢ ማስገኛ ከተሰራው ህንፃ በክልሉ በአስቸጋሪ የኑሮ ሁኔታ ውስጥ ለሚገኙና ጧሪ ለሌላቸው አንድ ሺህ 500 ሰዎች በየወሩ የ300 ብር ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል። በቀጣይም በአስቸጋሪ የኑሮ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ አረጋዊያንን ለመደገፍ በየዞኑ ተመሳሳይ የገቢ ማስገኛ ህንፃዎችን ለመገንባት ቀደም ሲል ቦታ የመረከብ ሥራ ተከናውኖ የዲዛይን ሥራቸው በመከናወን ላይ መሆኑን አመልክተዋል። ለገቢ ማስገኛ ህንጻዎች ግንባታ ማስጀመሪያ የሚሆን 150 ሚሊዮን ብር በቴሌቶን ለማሰባሰብ የሚያስችል የማስጀመሪያ መርሀግብር በይፋ መጀመሩንም ዛሬ በበዓሉ ላይ አብስረዋል። አረጋዊያን በሁሉም አካባቢ በማህበር ተደራጅተው በመንቀሳቀስ ተሳታፊና ተጠቃሚነታቸውን እንዲያረጋግጡም ቢሮው ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ነው ዶክተር ሞላ ያስረዱት። "አረጋዊያን ለትውልድ የሚያስተላልፉት የዕምቅ ሃብት ባለቤቶች ናቸው" ያሉት ደግሞ በበዓሉ ላይ የተገኙት የክልሉ ምክር ቤት ምክትል አፈጉባኤ ወይዘሮ ትልቅሰው ይታያል ናቸው። አረጋዊያን በዕድሜ ዘመናቸው ያካበቱትን ዕምቅ የዕውቀት ሃብት ለወጣቱ ትውልድ በማካፈል ለሀገር ልማት እንዲያውሉና ተጠቃሚነታቸው እንዲረጋግጥ ሁሉም ሊያግዛቸው እንደሚገባም አስገንዝበዋል። "አረጋዊያንም ሀገራዊ ለውጡ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የነበረውን የህዝቦች አብሮነት፣ መረዳዳት፣ የተጣላን የማስታረቅና የተራራቁትን የማቀራረብ እሴት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ለወጣቱ ትውልድ ማስተማር አለባቸው" ብለዋል። የክልሉ ምክር ቤትም የሀገር ባለውለታ በሆኑ አረጋዊያን ላይ የሚደርሱ የመብት ጥሰቶችን ለመከላከል የሚያደርገውን የክትትልና ቁጥጥር ሥራ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ቃል ገብተዋል ወይዘሮ ትልቅሰው። በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሶሻል ወርክና ሲቪል ዲቨሎፕመንት መምህር የሆኑት ዶክተር ሳምሶን ጫኔ ባቀረቡት ጽሁፍ አረጋዊያን መብትና ጥቅሞቻቸውን ለማስከበር አደረጃጀታቸውን ማጠናከር እንዳለባቸው አመልክተዋል። ለአደረጃጀታቸው ትኩረት ካልተሰጠ ለከፋ ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ ችግር እንደሚጋለጡ ገልጸው "ይህም በሀገር ኢኮኖሚ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ያሳድራል" ብለዋል። አረጋዊያንን የሚደግፉ አካላት በበቂ ሁኔታ አለመኖር ለጤና፣ ለመጠለያ፣ ለምግብና መሰል ችግሮች እያጋለጣቸው መሆኑን ተናግረው ችግሮቻቸውን ለማቃለል መንግስትና ህብረተሰቡ ድጋፍ ሊያደርግላቸው እንደሚገባ አስገንዝበዋል። "መጠለያ በማጣታቸው በየቤተ ዕምነቱ ተጠልለው በከፋ ችግር ውስጥ ኑሯቸውን የሚገፉ አረጋዊያን ከችግር እንዲወጡ ሊደገፉ ይገባል" ያሉት ደግሞ ከባህር ዳር ከተማ አረጋዊያን ማህበር አቶ ታደሰ አለማየሁ ናቸው። ከጎንደር ከተማ አረጋዊያን ማህበር የመጡት አቶ አለም በላይ በበኩላቸው ያሉባቸውን ውስብስብ ችግሮች ለይቶ መፍትሄ ለመስጠት የሚሰራው ስራ የሁሉንም አካላት ትኩረት እንደሚሻ አስረድተዋል። በክልሉ ከሚገኙ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን አረጋዊያን መካከልም ግማሽ ሚሊዮን የሚጠጉት በከፋ ድህነት ውስጥ የሚገኙ በመሆናቸው ዘላቂ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው በመድረኩ ተጠቁሟል። " ቀደምት የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችን በመዘከር የኢትዮጵያ አረጋዊያንን ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት እናረጋግጥ" በሚል መሪ ሃሳብ በዓሉ ለ28ኛ ጊዜ በባህር ዳር ከተማ ሲከበር ለ600 ሰዎች የቁሳቁስ ድጋፍ ተደርጓል። በበዓሉ ላይም ከባህር ዳርና ከክልሉ የተለያዩ ዞኖች የተውጣጡ አረጋዊያን ተገኝተዋል ።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም