በጋምቤላ ከተማ ወንጀሎችን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት የህብረተሰቡ ሚና መጠናከር አለበት... የከተማዋ ከንቲባ

59
ጋምቤላ ጥቅምት 25/2011 በጋምቤላ ከተማ የሚፈጸሙ የተለያዩ ወንጀሎችን ለመከላከል በሚደረገው ጥረት የሕብረተሰቡ ተሳትፎ መጠናከር እንዳለበት የከተማዋ ከንቲባ አሳሰቡ፡፡ የከተማዋ ነዋሪዎች ወንጀሎችን በጋራ መከላከል በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ከከተማው አመራሮች ጋር ትናንት ተወያይተዋል፡፡ በውይይት መድረኩ ላይ የተገኙት የከተማዋ ከንቲባ አቶ ቺቢ ቺቢ እንደገለጹት በከተማዋ በዜጎች ላይ ዘረፋ፣ በስለታማ መሳሪያዎች ጉዳት ማድረስና ሌሎች ወንጀሎች በተደጋጋሚ እየተፈጸሙ መሆኑ ተስተውሏል። እነዚህን ወንጀሎች ለመከላከል በሚደረገው ጥረት የከተማዋ ነዋሪዎች ለሰላም ዘብ በመቆም ተሳትፏቸውን ማጠናከር እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡ በተለይም ወንጀል ፈጻሚዎችን አጋልጦ በመስጠት በኩል ህብረተሰቡ የሚያደርገውን ጥረት ሊያጎለብት እንደሚገባ ነው ያስገነዘቡት፡፡ የውይይቱ ዓላማም የከተማዋ ህብረተሰብ ሰላምን በማስጠበቅ በኩል የጠራ ግንዛቤ ይዞ የሚከሰቱ ወንጀሎችን ቀድሞ እንዲከላከል ለማስቻል መሆኑንም ከንቲባው አመልክተዋል፡፡ ከተማ አስተዳደሩ የከተማዋን ፀጥታ ለማስጠበቅና ሕብረተሰቡም ያለምንም የደህንነት ስጋት እንዲንቀሳቀስ ለማስቻል ከህብረተሰቡ ጋር ተቀራርቦ እንደሚሰራ አመልክተዋል፡፡ የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው በከተማዋ እየተፈጸሙ ያሉ ህገ ወጥ ድርጊቶችን ለመከላከል ከመንግስት ጎን በመሆን የድርሻቸውን ለመወጣት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡ ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል አቶ ኡቶው አኳይ በሰጡት አስተያየት "የከተማዋን ብሎም የክልሉን ሰላም ለማስጠበቅና ወንጀሎችን ለመከላከል ሁላችንም የድርሻችንን መወጣት አለብን" ብለዋል፡፡ መንግስት የወንጀል ድርጊቶችን ቀድሞ ለመከላከልና ለመቆጣጠር በሚያደርገው እንቅስቃሴ ህብረተሰቡን ከማስገንዘብ ጀምሮ ንቁ ተሳታፊ በማድረግ ሊሰራ እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡ "በከተማዋ የሚከሰቱ ወንጀሎችን ለመከላከል መንግስት ህገ ወጥ የጦር መሳሪያዎችን በመፈተሽ ችግር ፈጣሪዎችን መለየት ይኖርበታል" ያሉት ደግሞ ሌላው የውይይቱ ተሳታፊ አቶ ሉክ ጉር ናቸው፡፡ በየአካባቢያቸው የሚታዩ ለሰላም ጠንቅ የሆኑ እንቅስቃሴዎችን ሲያስተውሉ ለሚመለከታቸው አካላት በማሳወቅ የበኩላቸውን እገዛ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል። "በከተማዋ እየተፈጸሙ ያሉ ወንጀሎችን ለመከላከል በህብረተሰቡ መካከል ያሉ ልዩነቶችን ማጥበብና አመራሩም እራሱን የማጥራት ይኖርበታል" ያሉት ደግሞ ሌላው የውይይቱ ተሳታፊ አቶ ኡቦንግ ጋሜ ናቸው፡፡ "የከተማዋ ህብረተሰብ ወንጀለኞችን ከመደበቅ ይልቅ ለህግ አጋልጦ በመስጠት ለከተማዋ ሰላም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል፤ እኔም ለእዚህ እሰራለሁ" ብለዋል። በውይይቱ ላይ የከተማዋ ነዋሪዎች፣ የፀጥታ አካላትና አመራሮች ታድመዋል ሲል የዘገበው የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ነው፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም