የዘንድሮው የብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች በዓል ሲከበር ኢትዮጵያዊ አንድነት በማረጋገጥ መሆን እንዳለበት ተገለጸ

74
አዲስ አበባ ጥቅምት 25/2011 የዘንድሮው የብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች በዓል ሲከበር በብዝሃነት ላይ የተመሰረተውን ኢትዮጵያዊ አንድነት በማረጋገጥ መሆን እንዳለበት ተገለጸ። 13ተኛው የብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በአዲስ አበባ የሚከበር ሲሆን የበዓሉን አከባበር አስመልክቶ የበዓሉ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ከሚመለከታቸው ባለደርሻ  አካላት ጋር በመሆን በበዓሉ የአከባበር  ዙሪያ በተዘጋጀ እቅድ ላይ ውይይት አድርጓል። የበዓሉ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ነስረዲን መሃመድ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፣ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ የምትሰኘው በብሄር ብሄረሰቦቿ በመሆኑ ህዝቦች በብዝሃነት ላይ የተመረኮዘውን ኢትዮጵያዊ አንድነታችንን ለማጠናከር  መስራት አለብን። የብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን ሲከበር እስካሁን በነበረው ሄደት በአብዛኛው የተሰራው ከብሄር ማንነት ጋር የነበረ ሲሆን አሁን ግን ያንን በሚያስታርቅ መልኩ በብዝሃነት ውስጥ የሚታይ ኢትዮጵያዊ  አንድነትን የሚያጎላ በዓል ይሆናል ብለዋል። የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ወይዘሮ  አበበች ነጋሽ በበኩላቸው፣ በዓሉ አገሪቷ በትልቅ ለውጥ ውስጥ ባለችበት በአሁኑ ወቅት መከበሩ መልካም አጋጣሚ በመሆኑ በዓሉ ሲከበር በህዝቦች የአስተሳሰብ ለውጥ ላይ ያተኮረ መሆን አለበት ብለዋል። ልዩነታችን አንድነታችንን የሚያጠናክር በመሆኑ፣ አልፎ አልፎ እዚህም እዚያም የሚስተዋሉትን ግጭቶች በአስተሳሰብ ቀረጻ በኢትዮጵያዊነት የአንድነት ስሜት ልንፈታ ይገባል ብለዋል። በመጪው ህዳር በሚከበረው የብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች  በዓል ላይ አዲስ አበባ በአዘጋጅነት ስትሰናዳ  የሁሉም ብሄረሰቦች መዲና በመሆኗ  እስካሁን ከተከበሩት የበዓሉ አከባበር  ልምድ በመውሰድ በተሻለ አቀራረብ ለመታየት እየተሰራበት መሆኑም ተገልጿል። በእቅድ ውስጥ  ከተያዙት መርሃ ግብሮች ውስጥ ፣ የፓናል ውይይቶች አንዱ ሲሆን በዚህም የሃይማኖት አባቶች፣ የወጣቶችና የሴቶች መድረክ ይኖራሉ ተብሏል። በሚሊኒየም አዳራሽ በ10ሺህ ህጻናት ህብረ ብሄራዊነት ምንድነው፣ ህገ መንግስቱ ያጎናጸፈን መብት ምንድነው በሚል እሳቤ በኪነጥበባዊ መንገድ የሚሰሩ ፕሮግራሞች እንደሚኖሩም ተገልጿል። ከሁሉም ክልሎች የተውጣጡ የ5ኛ ክፍል ተማሪ የሆኑ፣ በትምህርታቸውም ከ4ኛ ክፍል ወደ 5ኛ ክፍል ሲያልፉ 1ኛ የወጡትን አንድ ሴትና አንድ ወንድ ታዳጊዎችን ከነወላጆቻቸው አዲስ አበባን አንዲጎኙ  ይደረጋል። በዚህም  የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤትን ጨምሮ የከንቲባ ጽህፈት ቤትንና  የአፍሪካ ህብረትን እንዲጎበኙ ይደረጋል። በዘንድሮው የብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች  በዓል ላይ እንደሌላው ጊዜ ሁሉም የራሱን ብሄረሰብ ባህል ብቻ ማሳየት ሳይሆን ከወዲሁ እጣ በማውጣት አንዱ ብሄር የሌላውን ብሄር ጭፈራ አጥንቶ የዚያን ብሄር አልባሳት ለብሶ ፣ በበዓሉ እንዲታደም ይደረጋልም ተብሏል። 'ኑ ለሰላም ቡና እንጠጣ' በሚል የተዘጋጀና  10 ሺህ ሰዎችን የሚያሳትፍ ልዩ ፕሮግራም እንዳለም ተገልጿል። የሰላም ፕሮቶኮል መዝገብ ማዘጋጀትም የበዓሉ አካል ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ሃሳባቸውን ካሰፈሩ በኋላ ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎችም ሃሳባቸውን ከሰላምና አጠቃላይ አገራዊ እንድምታ አንጻር እንድያሰድሩበት ይደረጋል። በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ሁሉም ኢትዮጵያዊ መሳተፍ በሚያስችለው መልኩ በምርጥ የባህላዊ አለባበስ የፎቶ ውድድርም ይኖራል። የዶክመንተሪ ፍልም ተሰርቶ በበዓሉ ዋዜማ በተለያዩ ሚዲያዎች አንዲለቀቁም ይደረጋል። በእቅዱ የተካተቱ በርካታ ሃሳቦች ሲኖሩ በዓሉን ከምን ጊዜውም በላይ ፍሬያማና የተሳካ እንዲሆንና አገራዊ አንድነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ለማድረግም ሰፊ ዝግጀት እየተደረገ ነው ተብሏል። የብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች በዓል ከዚህ በፊት በአገር አቀፍ ደረጃ ለ12 ጊዜ የተከበረ ሲሆን በመጪው ህዳር የሚከበረው  ለ13ተኛ ጊዜ ይሆናል።                  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም