የተቋረጠው የመጠጥ ውሃ ቢለቀቅም በአካባቢያችን ባለመድረሱ ተቸግረናል...በሐረር ከተማ አንዳንድ ነዋሪዎች

59
ሐረር ጥቅምት 25/2011 በሐረር ከተማ ተቋርጦ የነበረው የንጹህ መጠጥ ውሃ ተለቋል ቢባልም እስካሁን ውሃ በአካባቢያቸው ባለመድረሱ መቸገራቸውን በከተማው አንዳንድ ቀበሌ የሚገኙ ነዋሪዎች ገለጹ። የክልሉ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን በበኩሉ በከተማው የንጹህ መጠጥ ውሃን ለሁሉም ቀበሌ ነዋሪዎች ለማዳረስ አቅም በፈቀደ መልኩ እየተሰራ መሆኑን  አስታውቋል። አስተያየታቸውን ለኢዜአ ከሰጡ ነዋሪዎች መካከል በከተማው ቀበሌ 13 ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ጽጌ አለሙ ንጹህ የመጠጥ ውሃ ካጡ አንድ ወር እንደሞላቸው ተናግረዋል። "በአሁኑ ወቅት 'ድሬ ጠያራ' ከሚባል አካባቢ አንድ ጀሪካን ውሃ እስከማምጫው በ15 ብር እየገዛን በመጠቀም ላይ እንገኛለን፤ ይህ ደግሞ በኑሯችን ላይ ተጽዕኖ እየፈጠረብን ይገኛል" ብለዋል። "ተቋርጦ የነበረው ውሃ ተለቋል የሚል መረጃ ቢደርሰንም ወደእኛ አካባቢ ሊመጣ አልቻለም፤ ምክንያቱ ምን እንደሆነ ባይገባንም የሚመለከተው የመንግስት አካል ፈጣን መፍትሄ ይስጠን" ሲሉ ጠይቀዋል። ንጹህ የመጠጥ ውሃ ፍለጋ የሚያባክኑት ጊዜ የሥራ ሰዓታቸውን እየተሻማባቸው መሆኑን የገለጹት ወይዘሮ መሰረት ብርሃኑ የተባሉ ነዋሪ በበኩላቸው፣ ገዝተው የሚጠቀሙት ውሃ በጤናቸው ላይ ጉዳት እያስከተለባቸው መሆኑን ገልጸዋል። "በከተማው ተቋርጦ የነበረው ውሃ መለቀቁን ብንሰማም እስካሁን ምንም አላየንም፤ በውሃ ስርጭቱ ላይ ያለው ችግር ተፈቶ ለሁላችንም ፍትሃዊ የውሃ ክፍፍል እንዲኖር እንፈልጋለን " ሲሉ ቅሬታቸውን አቅርበዋል። "በከተማው የተፈጠረው የውሃ እጥረት ስራዬን እንዳቋርጥ አድርጎኛል፤ ለቤትውስጥ ፍላጎት ውሃ ለማቅረብ እንኳ በቀላሉ ማግኘት አልቻልኩም" ያሉት ደግሞ በኮንስትራክሽን ሥራ ዘርፍ የተሰማሩት አቶ መብራቱ አምደማርያም ናቸው። ችግሩ አሳሳቢ ደረጃ ላይ በመድረሱ የሚመለከተው አካል መፍትሄ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል ። በሐረር ከተማ ቀበሌ 18 የሚኖሩትና በአነስተኛ የምግብ ንግድ ሥራ የተሰማሩት አቶ መሀመድ አሊ ውሃ በሳምንት አንድ ቀን ብቻ ማግኘታቸውን ተናግረዋል። "የሆቴልና የምግብ አገልግሎት ለሚሰጥ ተቋም የውሃ አቅርቦት እጥረት መኖር በስራው ላይ ተጽዕኖው ስለሚያሳድር መፍትሄ ይበጅለት" ብለዋል። የኢዜአ ጋዜጠኛ በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች ተዘዋውሮ እንደተመለከተው በተለይ በከተማው ቀበሌ 13 በተለምዶ "ቀላዳን" በሚባለው አካባቢ እንዲሁም ጀጎል፣ ቀበሌ 16 እና 15 የንጹህ መጠጥ ውሃ አለመድረሱን አረጋግጧል። በአንጻሩ በከተማው ቀበሌ 10፣18 እና 14 የንጹህ መጠጥ ውሃ በተያዘው ሳምንት ለአንድ ቀን መዳረሱን ነው ያረጋገጠው። የክልሉ ውሃና ፍሳሽ ባለስልጣን አቶ ተወልደ አብዶሽ በበኩላቸው በከተማው አቅም በፈቀደ መልኩ የንጹህ መጠጥ ውሃን ለሁሉም ቀበሌ ነዋሪዎች ለማዳረስ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል። ከድሬዳዋ አስተዳደር በተዘረጋ የውሃ መስመርና ከሐረማያ ከተማ በቦቴ መኪና በማመላለስ ለህብረተሰቡ ውሃ ለማቅረብ ጥረት ቢደረግም በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ውሃ ያልደረሰባቸው አካባቢዎች መኖራቸውን ተናግረዋል። በቀጣይ የንጹህ መጠጥ ውሃ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች ውሃውን በዙር የማዳረስ ሥራ በማከናወን ሁሉንም ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚሰራም አመልክተዋል። በክልሉ ኤረር ቂሌ ገበሬ ማህበር በአርሶ አደሩ በተነሱ ጥያቄዎች መስመሩ የተቋረጠው የኤረር ቂሌ የውሃ ፕሮጀክት ሥራን ለማስጀመር የክልሉ መንግስት፣ የጸጥታ አካላትና የወረዳው አስተዳደር ጥረት እያደረጉ መሆናቸውን ጠቁመዋል። ጥረቱ ተሳክቶ በአጭር ጊዜ መፍትሄ ካገኘ የክልሉ የንጹህ መጠጥ ውሃ ችግር ሙሉ ለሙሉ እንደሚቀረፍ አቶ ተወልደ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም