የእግር ኳስ ፌዴሬሽን የስራ ኃላፊዎች በወልዋሎና በመቐለ ጨዋታ ላይ ያሳዩት የስፖርታዊ ጨዋነት የማስፈን እንቅስቃሴ መቀጠል አለበት

65
አዲስ አበባ ጥቅምት 25/2011 ትናንት በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ሁለተኛ ሳምንት በመቐለ ስታዲየም ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርስቲና መቐለ ሰብኣ እንደርታ ጨዋታቸውን ማድረጋቸው ይታወቃል። በዚሁ ጨዋታ ላይ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ጅራና የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ምክትል ፕሬዚዳንት ኮሎኔል አወል አብዱራሂም ተገኝተዋል። ሁለቱ የፌዴሬሽኑ የስራ ሃላፊዎች ጨዋታው ከመጀመሩ በፊት በስታዲየሙ በመዞር ለደጋፊው ሰላምታ ማቅረባቸውንና ደጋፊው በስፖርታዊ ጨዋነት ላይ እንዲሰሩ ጥሪ እንዳቀረቡ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ዳንኤል ዘርአብሩክ ለኢዜአ ገልጸዋል። ጨዋታው ሲጠናቀቅ የባለሜዳው ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርስቲ ክለብ ደጋፊዎች ለመቐለ ሰብኣ እንደርታ ደጋፊዎች ሽኝት እንዳደረጉና ጨዋታው ሰላማዊ በሆነ መልኩ መጠናቀቁንም ተናግረዋል። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ከትግራይ እግር ኳስ ፌደሬሽን ጋር በመሆን በክልሉ በሚደረጉ ጨዋታዎች ስፖርታዊ ጨዋነት እንዲሰፍን  እንደሚሰራም አመልክተዋል። በሁለቱ ክለቦች ጨዋታ ላይ የትግራይ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ሃላፊና ምክትል ሃላፊ ተገኝተዋል። ዛሬም በሚደረጉ የሊጉ ጨዋታዎች መሰል ስፖርታዊ ጨዋነትን የተመለከቱ መልዕክቶች እንደሚተላለፉም ጠቅሰዋል። ዛሬ በአዲስ አበባ ስታዲየም ቅዱስ ጊዮርጊስ ከባህር ዳር ከተማ በሚያደርጉት ጨዋታ የፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ጅራ ተገኝተው እንደሚከታተሉም ጠቁመዋል። የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ በዘንድሮው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ስፖርታዊ ጨዋነት እንዲሰፍን አስፈላጊውን ጥረት እንደሚያደርግም ነው አቶ ደንኤል ያስረዱት። ባለፈው ዓመት በአዲግራት ስታዲየም ወልዋሎ አዲግራት ዩንቨርስቲና መቐለ ሰብኣ እንደርታ ባደረጉት ጨዋታ ላይ በደጋፊዎች መካከል ግጭት ተፈጥሮ በደጋፊዎች ላይ ጉዳት መድረሱ የሚታወስ ነው። የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን አዲሱ አመራር ውድድር በሚካሄድበት ወቅት የሚከሰተውን የሜዳ ላይ ስርዓት አልበኝነት ችግርን በመፍታት ስፖርታዊ ጨዋነትን ማስፈን ተቀዳሚ ተግባሩ እንደሆነ ሲገልጽ ቆይቷል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም