ኤጀንሲው ከ5 ሺህ 600 በላይ ለሚሆኑ የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን ስልጠና መስጠቱን አስታወቀ

64
መቀሌግንቦት 15/2010 የትግራይ አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ልማት ኤጀንሲ ከ5ሺህ 600 በላይ ለሚሆኑ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኮሌጅ ምሩቃን የሙያ ስልጠና መስጠቱን አስታወቀ። ስልጠናውን ከተከታተሉት ውስጥ  አንድ ሺህ የሚሆኑት ሴቶች ናቸው፡፡ ባለፉት 10 ወራት የተሰጠው ስልጠና ያተኮረው በኢንተርፕሪነርሺፕ፣ በካይዘን የአመራር ፍልስፍና፣ በተለያዩ አዳዲስ የቴክኖሎጂ ውጤቶችና በሌሎች ተጓዳኝ የሙያ ዘርፎች  መሆኑን የኤጀንሲው የህዝብ ግንኙነት ተጠባባቂ ኃላፊ ወይዘሮ ቅድስት ጻዕዱ ተናግረዋል። ወጣቶቹ በመረጡት የሙያ ዘርፍ በመሰልጠን በአሁኑ ወቅት ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በተለያዩ ተቋማትና በግላቸው ወደስራ መሰማራታቸውን ገልፀዋል፡፡ የስራ እድል ከተፈጠረላቸው የከፍተኛ ትምህርት ምሩቃን መካከል ወጣት አስፋው በየነ በሰጠው አስተያየት በኤጀንሲው በተሰጠው የሙያ ስልጠና ተጨማሪ ክህሎትና እውቀት በማግኘቱ በውቅሮ ሸባ ቆዳ ፋብሪካ በወር 3 ሺህ ብር ደሞዝ ተቀጥሮ በመስራት ላይ መሆኑን ገልጿል፡፡ ወጣት ምህረት ተስፉ በበኩሏ በኬሚካል ኢንጅነሪንግ ተመርቃ ስራ ሳትይዝ ለስድስት ወራት መቆየቷን ተናግራለች። በኤጀንሲው ባገኘችው  የሙያ ስልጠና ድጋፍ በመቀሌ ከተማ በሚገኘው የጨርቃ ጨርቅ ፋብሪካ በወር 4 ሺህ 500 ብር ተቀጥራ እየሰራች መሆኑን ገልጻለች። በተሰጣት የሙያ ስልጠና ድጋፍ ለስራዋ የሚያገለግላት ተጨማሪ ግብአት ማግኘቷንና ባገኘችው ስራም ደስተኛ መሆኗን ተናግራለች። ሌሎች የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ምሩቃንም የስራ ዘርፍና ቦታ ሳይመርጡ በተለያየ የልማት ዘርፎች ተሰማርተው ራሳቸውን በመጥቀም የአከባቢያቸውን ልማት እንዲያፋጥኑ ጠቁማለች።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም