የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የእምቦጭ አረምን ለማስወገድ ያሰራቸውን ማሽኖች አስመረቀ

130
ባህር ዳር ጥቅምት 25/2011 የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በጣና ሐይቅ ላይ የተከሰተውን የእምቦጭ አረም ለማስወገድ የሚያግዙ አራት ማሽኖችን በ19 ነጥብ 2 ሚሊዮን ብር ወጪ አስርቶ አስመረቀ። ማሽኖቹ ዛሬ የተመረቁት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው፣ የዩኒቨርሲቲው ምሁራንና የአካባቢው ማህበረሰብ በተገኙበት ነው። ለምረቃ የበቁት ማሽኖች የጣናን የጥልቀት መጠን ከግምት ውስጥ ያስገቡ ሲሆኑ እምቦጩን ለመሰብሰብ፣ የተሰበሰበውን የሚያጓጉዙና ከሐይቁ ዳርቻ የሚያወጡ መሆናቸውም በምረቃው ላይ ተገልጿል። የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በእዚህ ወቅት እንዳሉት የእምቦጭ አረምን ከጣና ሐይቅ ላይ ለማስወገድ የሰው ጉልበት ከመጠቀም በተጨማሪ የአርሶ አደሩን ጉልበት የሚያግዙ ማሽኖችን በመጠቀም አረሙ በሐይቁ ላይ የፈጠረውን ስጋት ለመከላከል እየተሰራ ነው። "ጣና ሐይቅ የኢትዮጵያ ብሎም የክልሉ ሀብት በመሆኑ የሚመለከታቸው አካላት በእውቀት፣ በገንዘብና በጉልበት ድጋፍ ሊያደርጉ ይገባል" ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል። የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ፍሬው ተገኝ በበኩላቸው ጣና ሐይቅን ከእምቦጭ አረም ለመከላከል ተቋሙ ካሰራቸው ማሽኖች በተጨማሪ በምርምር የታገዘ ድጋፍ ለማድረግ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም